አዲስ አበባ፣ የካቲት 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሶማሊያ ሞቃዲሾ ሲደርሱ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሀመድ ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ሁለቱ መንግስታት በጋራ ባወጡት የአቋም መግለጫ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የሥራ ጉብኝት ባለፉት ጊዜያት በሀገራቱ መካከል ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደነበረበት የመመለስ ጥረት አካል እንደሆነ ተገልጿል።
መሪዎቹ ግንኙነቱን በማጠናከር ለጋራ ተጠቃሚነት ለመስራት ያላቸውን ቁርጠኝነት አሳይተዋል።
ሀገራቱ የሚያገናኛቸውን ድንበር እና የህዝብ ለህዝብ ታሪካዊ ግንኙነታቸውን ተገቢውን ዕውቅና በመስጠት በዲፕሎማሲያዊ፣ በኢኮኖሚ እና በማህበራዊ ትብብር ያላቸውን ትብብር ማሳደግ እንዳለባቸውም ተመላክቷል።
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በቀጣናዊ መረጋጋትና ብልጽግና የጋራ ግብና ራዕይ ያላቸው የተሳሰሩ ሀገሮች መሆናቸውን የጠቀሰው የጋራ መግለጫው፥ በዚህም ሁለቱ መሪዎች ስትራቴጂክ የመሰረተ-ልማት ፕሮጀክቶችን ለመተግበር ቁርጠኝነት እንዳላቸው ገልጿል።
ይህም የሀገራቱ እድገት ቀጣይነት እንዲኖረው፤ የኢኮኖሚ ትብብርና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲረጋገጥ ያደርጋል ተብሏል፡፡
በተጨማሪም በአንካራ ስምምነት መሰረት የቴክኒካል ውይይቶች ተጀምረው በስምምነቱ መሰረት እየተካሄዱ መሆኑ መሪዎቹ እንደሚቀበሉትና ውይይት እንዲሁም ትብብር ለማድረግ ያላቸውን ቁርጠኝነት አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሠራዊትና በሶማሊያ ብሔራዊ ጦር ሠራዊት አዛዦች መካከል የተደረገውን መግባባትም የፀጥታ ትብብርን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስና በቀጣናው መረጋጋትን ለማምጣት ወሳኝ እርምጃ መሆኑን በመገንዘብ በደስታ ተቀብለዋል ብሏል መግለጫው።
ሁለቱ ወገኖች የጋራ ጥቅሞችን በማሳደግ፣ ሰላምና ደህንነትን በማስፈን እንዲሁም የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን በማጠናከር ለዜጎቻቸውና ለአጠቃላይ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል ተብሏል።