Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የጋራ ዓላማችንን ለማሳካት በትብብር መስራት ይጠበቅብናል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ የካቲት 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የጋራ ዓላማችንን ለማሳካት በትብብር መስራት ይጠበቅብናል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ዛሬ በወንድሜ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሃመድ ለተደረገልኝ ደማቅ አቀባበል አመሰግናለሁ ብለዋል።

በቆይታዬ በሰላምና ጸጥታ፣ ኢኮኖሚ፣ ዲፕሎማሲ እና የተቀናጀ መሰረተ-ልማት ግንባታን ጨምሮ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት አድርገናል ብለዋል።

የአፍሪካ ቀንድ በተፈጥሮ ሃብት የታደለ ነው፤ ለም መሬት፣ ንጹህ ውሃ እና የሰው ሃብት አለው ሲሉም ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ እንደ ቀጣና ራሳችንን ለመመገብ ትግል እያደረግን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ የጋራ ዓላማችንን ለማሳካት በትብብር መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

እንደቀጣና የጋራ ህልማችንን እውን ለማድረግ የሚያስችል እምቅ አቅም አለን፤በተናጠል እንደማናድግ በመገንዘብ በትብብር ለመበልጸግ መስራት ይጠበቅብናል ሲሉ አስገንዝበዋል።

ቀጣናዊ አስተሳሰብ እና በትብብር መስራት ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበው፤ዕድገትና ብልጽግናን የማምጣት ህልማችንን እውን ለማድረግ ከሶማሊያ ጋር በትብብርና በቅንጅት ለመስራት ዝግጁ ነን ብለዋል።

Exit mobile version