አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር ያሳዩትን ቁርጠኝነት አደነቀ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በትናንትናው ዕለት በሶማሊያ ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ ሁለቱ ሀገራት ግንኙነታቸውን ለማጠናከር መስማማታቸውን አስታውቀዋል፡፡
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ÷ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር ያሳዩትን ቁርጠኝነት አድንቋል፡፡
ኢትዮጵያና ሶማሊያ ለቀጣናዊ ትብብር እና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ያሳዩት ቁርጠኝነት የሚበረታታ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥቷል፡፡
ሀገራቱ ከአንካራው ስምምነት ወዲህ በመሪዎች ደረጃ ያደረጓቸው ውይይቶችና ስምምነቶች ለኢኮኖሚያዊ ትብብርና ለቀጣናው መረጋጋት ወሳኝ ርምጃዎች ናቸው ሲል አስገንዝቧል፡፡
ኢጋድ ሰላማዊ ግንኙነቶችን የሚያጠናክሩ እና ለቀጣናው ዘላቂ ልማት የሚደረጉ ጥረቶችን እንደሚደግፍም አረጋግጧል፡፡

