Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት የአባልነት ሂደትን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ ቁርጠኛ መሆኗን ገለጸች

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት የአባልነት ሂደትን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ ቁርጠኛ መሆኗን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ገለጹ።

በዋሽንግተን ዲሲ እየተካሄደ ካለው የዓለም ባንክና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ዓመታዊ የፀደይ ወቅት ስብሰባ ጎን ለጎን የኢትዮጵያና ኡዝቤኪስታን የዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት ሂደትን የተመለከተ የከፍተኛ ደረጃ ውይይት ተካሂዷል።

ሚኒስትር ዴኤታው በዚሁ ወቅት፥ የኢትዮጵያን የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ስኬትና ማዕቀፉ ለኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት ጥያቄ ያለውን አንድምታ አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ በቀጣዩ ዓመት አጋማሽ በካሜሮን ያውንዴ በሚካሄደው 14ኛው የዓለም የንግድ ድርጅት የሚኒስትሮች ስብስባ ላይ አባል የመሆኗን ሂደት ለማጠናቀቅ በቁርጠኝነት እንደምትሰራም ገልጸዋል።

የዓለም የንግድ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ንጎዚ ኦኮንጆ-ኢዊላ በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያና ኡዝቤኪስታን የአባልነት ሂደት እንዲፋጠን የባለብዝሃ ወገን ተቋማትና የሁለትዮሽ አጋሮች አስፈላጊውን የቴክኒክና የአቅም ግንባታ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

በመድረኩ ላይ የተሳተፉ የዓለም ባንክና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም የሥራ ኃላፊዎች፡ ኢትዮጵያ ህግን መሰረት ባደረገው የዓለም የንግድ ስርዓት አካል ለመሆን ያሳየችውን ቁርጠኝነት አድንቀዋል፡፡

ለኢትዮጵያ የአባልነት ሂደት ሙሉ ድጋፋቸውን እንደሚሰጡም መግለጻቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

Exit mobile version