Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን መርቀው ከፈቱ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በዛሬው ዕለት መርቀው ከፍተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ ዜጎቻችን ላይ ምሬት የሚፈጥሩ አሰራሮችን ፈትሾ ማስተካከል ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ ነው ብለዋል።

ለዚህ ቁርጠኝነታቸን አንዱ ማሳያ የሆነውን የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ዛሬ መርቀናል ሲሉ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን አዲስ ማዕከል ከሚገልጡ ሶስት ቁልፍ አላባውያን መካከል የቆየና የተጎዳ ህንፃን ወደ ዘመናዊና ሥነ-ውበታዊ ደረጃው ለሥራ ከባቢ አስደሳች ወደሆነ ህንፃ መለወጥ አንዱ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

አገልግሎቶችን ለመሰተርና ለማቀናጀት በሀገር ውስጥ የለማ ሶፍትዌር በሥራ ላይ መዋሉ ብሎም በታደሰ አመለካከት ብቁና ክብር የሞላበት አገልግሎት የሚሰጡ ወጣቶች መዘጋጀታቸው ሌሎቹ አላባውያን ናቸው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው 12 ተቋማት በአንድ ጣሪያ ሥር 40 የተለያዩ አገልግሎቶችን መስጠት መጀመራቸውን ገልጸው፥ ዜጎች ጊዜያቸውን እንዲቆጥቡና አገልግሎቶችን በተሻለ ውጤታማ መንገድ ለማግኘት እንደሚያግዝ አመልክተዋል።

አክለውም እንደዚህ ያሉ ሥርዓቶችን ማበልፀግ ለዜጎች የተለያዩ የአገልግሎት ርካታ መታጣቶች ምላሽ በመስጠት በሂደት ለሰፊው ማኅበረሰብ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ጠቁመዋል።

የዛሬው ምረቃ ትልቅ ርምጃ መራመዳችንን የሚያሳይ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ኢትዮጵያ በዚህ ማዕከል ላይ ጨምራና አስፋፍታ ለዜጎች ሁሉ የተሻለ የአገልግሎት አሰጣጥን ታረጋግጣለች ብለዋል።

Exit mobile version