አዲስ አበባ፣ ነሐሴ1፣2012 ( ኤፍ.ቢ.ሲ) የደቡብ ክልል ምክር ቤት 5ኛ ዙር 5ኛ አመት የስራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ጉባኤ በሀዋሳ መካሄድ ጀምሯል።
የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሄለን ደበበ የዘመናት የህዝቦች ጥያቄና ቁጭት የሆነው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ወደ ውጤት መቃረብና የመጀመሪያ ሙሌት በስኬት በመጠናቀቁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
የሀገራችንን ለውጥ ለመቀልበስ የፖለቲካና የግጭት መንገድን በመቀላቀል የሚንቀሳቀሱ ሀይሎች ሁሉም ዜጋ ሊታገላቸው ይገባል ያሉት አፈ ጉባኤዋ መንግስትም ሆነ የምክር ቤት አባላት የዜጎችን ደህንነት በማስጠበቅ ረገድ በንቃት ሊንቀሳቀሱ እንደሚባም ተናግረዋል ፡፡
መንግስት በተቋማት ግንባታ ላይ በመረባረብ ዘላቂና አስተማማኝ የህዝብ ተጠቃሚነትን ሊያረጋግጥ እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል።
የክልሉ መንግሥት የህዝቡን የአደረጃጀት ጥያቄዎች ለመመለስ እየሰራ መሆኑን ያነሱት አፈ ጉባኤዋ በዚህ ሂደት ውስጥ የሚታዩ አፍራሽ መልዕክቶችን መመከት ይገባል ማለታቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ምክር ቤቱ በ3 ቀናት ቆይታው በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ውይይት በማድረግ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል ።

