አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢንዱስትሪው ዘርፍ የኢኮኖሚ ሽግግር እንዲያመጣና የልማት ጉዞውን በስኬት እንዲያጠናቅቅ ለማድረግ ፖሊሲና ስትራቴጂ ተነድፎ በውጤታማ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን በኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ 2017 የማጠቃለያ መርሐ ግብር ላይ ንግግር አድርገዋል፡፡
በዚሁ ጊዜም የኤክስፖው ዓላማ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን ዕምቅ ዐቅም ለማሳየት፣ የእርስ በርስ ትሥሥር ለመፍጠር፣ ምርታቸውን ለማስተዋወቅ፣ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን ለማስተዋወቅ እንዲሁም ለፖሊሲና ስትራቴጂ ማሻሻያ የሚጠቅሙ ሐሳቦችን ለማሰባሰብ እና የኅብረተሰቡን በሀገር ምርት የመኩራት ባህል ለማሳደግ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያን የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች መካከል የአምራች ኢንዱስትሪው አንዱ መሆንም አስረድተዋል፡፡
ዘርፉ የኢኮኖሚ ሽግግር እንዲያመጣና የልማት ጉዞውን በስኬት እንዲያጠናቀቅ የተለያዩ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በመንግሥት ተነድፈው እየተሠሩ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡
በተጨማሪም የንግድ ሚዛን ጉድለትን ለማስተካከል፣ የሥራ ዕድል ለመፍጠርና በአጠቃላይ የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል ታልሞ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተፈጠረው መነሣሣትና የተቀናጀ አሠራር ምክንያት፤ የአምራች ኢንዲስትሪው አማካይ የማምረት ዐቅም አጠቃቀም በ2014 ከነበረበት 46 በመቶ በ2017 ግማሽ ዓመት 61 ነጥብ 2 በመቶ ደርሷል ብለዋል፡፡
የሀገር ውስጥ የገበያ ድርሻ በ2014 ከነበረበት 30 በመቶ በ2017 ዘጠኝ ወራት 41 ነጥብ 4 በመቶ ማድረስ መቻሉንም ጠቅሰዋል፡፡
የዘርፉ ዓመታዊ ዕድገት በ2014 ከነበረበት የ5 በመቶ ዕድገት በ2016 በጀት ዓመት በ10 ነጥብ 1 በመቶ ማደግ መቻሉን ገልጸው፤ በ2017 በጀት ዓመት 13 በመቶ ዕድገት እንደሚያስመዘግብ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም በተለያዩ ምክንያቶች ተዘግተው የነበሩ 837 ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ መግባታቸውን ገልጸዋል፡፡
ከ13 ሺህ 830 በላይ አዳዲስ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች እንዲቋቋሙና እንዲስፋፉ መደረጉንም ጠቅሰዋል፡፡
ንቅናቄው ከተጀመረ ጀምሮ 325 ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት መግባታቸውን ያነሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን፤ በዚሁ ዘርፍ በተሠራው ሥራ 910 ሺህ ቋሚ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል ብለዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ከተካሄዱት ኤክስፖዎች የ2017 የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ በብዙ መንገድ መለወጡን ጠቁመው፤ ለአብነትም የተሳታፊ አምራች ኢንዱስትሪዎች እና ያቀረቡት የምርት ዓይነት መጨመሩን አንስተዋል፡፡
የለውጡ መንግሥት አካሄድ ጀምሮ መጨረስ መሆኑን ገልጸው፤ እናልማለን፣ እናቅዳለን፣ በፍጥነትና በፈጠራ ያቀድነውን እናሳካለን ሲሉ በንግግራቸው አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ በትናንት እና በዛሬ መካከል ያለው ልዩነት የቀን ቁጥር ልዩነት ብቻ አይደለም፤ የዕለት ስያሜ ልዩነት ብቻም አይደለም፤ ልዩነቱ የብልጽግና ነው ሲሉም አስረድተዋል፡፡
ትናንት ኢትዮጵያን አይቶ ዐውቃታለሁ ማለት እንደማይቻል በማንሳት፤ ሠርክ አዲስ ናት፤ ተለውጣ ታድራለች፤ ምርቷ ይጨምራል፤ አሠራሯ ይቀየራል፤ ከተሞቿ ይለዋወጣሉ ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በለይኩን ዓለም