Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በአዲሷ የኢኮኖሚ ማዕከል ኢትዮጵያ ኢንቨስት ማድረግ አዋጭ ነው- ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በቂ የሰው ኃይልን ጨምሮ በርካታ የኢንቨስትመንት ዕድሎች ያሏት አዲሷ የኢኮኖሚ ማዕከል ናት ሲሉ የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያድርጉ 2025 የቢዝነስ ፎረም ላይ ሚኒስትሯ ባደረጉት ንግግር፤ በፍጥነት በማደግ ላይ ካሉ የዓለም ሀገራት አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ፤ በርካታ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዳሏት አብራርተዋል፡፡

ኢትዮጵያን ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ከሚያደርጓት ምቹ ሁኔታዎች አንዱ ከአጠቃላይ የሕዝብ ቁጥሯ 54 ሚሊየኑ ወጣት እና የሰለጠነ የሰው ኃይል መሆኑ ነው ብለዋል፡፡

ከሰሃራ በታች ካሉ ሀገራት 5ኛ ባለግዙፍ ኢኮኖሚ መሆኗም ተጨማሪ ዕድል መሆኑን አንስተው፤ ለአብነትም ባለፈው ዓመት 8 ነጥብ 1 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቧን አንስተዋል፡፡

የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ከመሳብ አንጻርም በፈረንጆቹ 2023/24 3 ነጥብ 9 ቢሊየን ዶላር መሳብ መቻሏን እና ይህም ከምሥራቅ አፍሪካ ቀዳሚ እንዳደረጋት ጠቅሰዋል፡፡

የግብርናው ዘርፍ ባለፈው ዓመት በ6 ነጥብ 9 በመቶ፣ የኢንዱስትሪ ዘርፉ 9 ነጥብ 2 በመቶ፣ የአገልግሎት ዘርፉ 7 ነጥብ 7 በመቶ ዕድገት ማስመዝገባቸውንም አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላት ስትራቴጂካዊ አቀማመጥ እንዲሁም ዓለምን የሚያካልለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ እንደሚያደርጓትም አስገንዝበዋል፡፡

እንዲሁም ኢትዮጵያ የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ሀገራት የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) መሥራች መሆኗ የ560 ሚሊየን ሕዝብን የገበያ አማራጭ ማግኘት ያስችላታል ነው ያሉት፡፡

በኢትዮጵያ የሚገኙትን ከላይ የተጠቀሱ የኢንቨስትመንት ዕድሎች በመገንዘብ ዓለም አቀፍ ባለሃብቶች መዋዕለ-ነዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በአቤል ንዋይ

Exit mobile version