Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኢትዮጵያ የቀጣናውን ሰላም ለማስጠበቅ የሚያስችል ሪፎርም እያደረገች መሆኗ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ከሀገር ባለፈ የቀጣናውን ሰላም እና ደኅንነት ለማስጠበቅ በሚያስችል መልኩ ተቋማዊ ሪፎርም እያደረገች መሆኗን የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጀኔራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ተናገሩ።

አምባሳደር ሬድዋን ይህን ያሉት ኢትዮጵያ እያስተናገደችው ባለው የአፍሪካ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ኮሚቴ የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ ስብሰባ ላይ ነው።

የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ባለፉት አስርት ዓመታት ውስጣዊ የሰላም ችግር፣ የባሕር ላይ ወንበዴዎች ዝርፊያ፣ የሳይበር ጥቃት፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር እና መሰል ፈተናዎች ማጋጠማቸውን አብራርተዋል፡፡

እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍም በትብብር መሥራት እንደሚገባ በአጽንኦት አንስተዋል፡፡

በዚህም የእኛ ኃላፊነት ከየሀገራችን ደኅንነት ጥበቃ ያልፋል ያሉት ዳይሬክተር ጀኔራሉ፤ ቀጣናዊ ሰላምን ማረጋገጥ ያስፈልገናል ብለዋል፡፡

የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት ተቋም ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ተቋማዊ ማሻሻያ እያደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ በሰው ሃብት በቴክኖሎጂ እና በክኅሎት ማሻሻል ላይ እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከስብሰባው በኋላም በጋራ ለመሥራት የሚያስችል አቋም እና አቅጣጫ እናስቀምጣለን ብዬ እጠብቃለሁ ነው ያሉት፡፡

በለይኩን ዓለም

Exit mobile version