አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የጃፓን መንግስት በአዲስ አበባ ከተማ የተላላፊ በሽታዎችን ሕክምና አገልግሎት ለማጠናክር የሚውል የ17 ነጥብ 4 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ አድርጓል፡፡
የድጋፍ ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ እና በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሺበታ ሂሮኖሪ ተፈራርመውታል፡፡
አቶ አሕመድ ሺዴ በዚህ ወቅት÷የጃፓን መንግስት የኢትዮጵያን የጤና ሥርዓት ለማዘመን ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የተደረገው ድጋፍ የሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ይበልጥ እየተጠናከረ መሆኑን እንደሚያሳይ አስገንዝበዋል፡፡
አምባሳደር ሺበታ ሂሮኖሪ በበኩላቸው÷የጃፓን መንግስት በኢትዮጵያ ለተለያዩ ዘርፎች የሚያደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
የተደረገው ድጋፍ ኢትዮጵያ የጤና ዘርፉን ለማዘመን የምታደርገውን ጥረት እንደሚያግዝ መግለጻቸውን በኢትዮጵያ የጃፓን ኤምባሲ ለፋና ዲጂታል አስታውቋል፡፡
በድጋፍ ስምምነቱ ወቅት የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ÷ድጋፉ ለቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አስፈላጊ የሕክምና ግብዓቶችን ለማሟላት እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ