Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አፍሪካ አህጉራዊ ባህልና አካታችነትን መሰረት ያደረገ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ልትገነባ ይገባል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አፍሪካ የሰው ሰራሽ አስተውሎትን አህጉራዊ ባህል እና አካታችነትን መሰረት ባደረገ መልኩ ልትገነባ ይገባል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን ለአፍሪካ ብልጽግና እና ትብብር” በሚል ሃሳብ እየተካሄደ ባለው “አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ለአፍሪካ” መርሐ-ግብር ላይ ተሳትፈዋል፡፡

መርሐ ግብሩን አስመልክተው በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷የቴክኖሎጂ ልህቀት ሽግግር ከቴክኖሎጂ ለውጥ እና ዝማኔ በላይ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

የቴክኖሎጂ ልህቀት ማለት የሰውን ልጅ የማሰብ ችሎታ ከረቀቁ ቴክኖሎጂዎች ጋር ማስተሳሰር ሲቻል ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ከዚህ አንጻር የሰው ሰራሽ አስተውሎት ባህልን ባከበረ መልኩ ከሰው ልጅ ችሎታ ጋር በመዋሃድ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት፡፡

ከቴክኖሎጂ ልህቀት አንጻር አፍሪካ ብዙ መስራት እንደሚጠበቅባት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ሌሎች ሀገራትን የሚያበረታታ እና አካታች የሆኑ የቴክኖሎጂ ሥራዎችን በመገንባት ረገድ አርአያ እየሆነች እንደምትገኝም አንስተዋል፡፡

Exit mobile version