Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ፋይዳ አማራጭ ሳይሆን አስፈላጊ መሠረተ ልማት ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ፋይዳ የዲጂታል ማንነት ሥርዓት ከአሁን በኋላ አማራጭ ሳይሆን አስፈላጊ መሠረተ ልማት ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው ዕለት የአይዲ ፎር-2025 ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤን በይፋ አስጀምረዋል፡፡
በጉባኤው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፥ በቅርብ ዓመታት ውስጥ፣ ዲጂታል ማንነት ተስፋ ሰጪ ከሆነው ፈጠራ ወደ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን መሠረታዊ ምሦሶ ተሻሽሏል ብለዋል።
ከአምስት ዓመት በፊት በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ራዕይ እየተመራን እጅግ አስፈላጊ ውሳኔ ወስነናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ይህም ዘመናዊ፣ አካታች፣ መሠረት ያለውና ሊሰፋ የሚችል ዲጂታል የማንነት ሥርዓት መገንባትና ለእያንዳንዱ ነዋሪ ተደራሽ ማድረግ መሆኑን ጠቁመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በመልዕክታቸው፥ ፋይዳ የዲጂታል ማንነት ሥርዓት ካርድ ብቻ ሳይሆን የግለሰቦችን ግላዊ መረጃዎች ምሥጢራዊነት በመጠበቅና አስፈላጊ የሆነውን ብቻ በማጋራት ማንነትን የሚያረጋግጥ ልዩ መለያ ቁጥር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ፋይዳ ከአሁን በኋላ አማራጭ ሳይሆን ሰዎችን ከአገልግሎቶች፣ ከማኅበረሰቦች፣ ከተቋማትና ከመንግሥታት ጋር የሚያገናኝ አስፈላጊ መሠረተ ልማት መሆኑንም አስረድተዋል።
Exit mobile version