Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

አይዲ ፎር አፍሪካ ቁርጠኛ የፓን አፍሪካ እንቅስቃሴ ነው – የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አይዲ ፎር አፍሪካ ጠንካራና ኃላፊነት የሚሰማቸው የማንነት ዐውዶችን በመገንባት የአፍሪካ ሀገራትን ለመደገፍ ቁርጠኛ የሆነ የፓን አፍሪካ እንቅስቃሴ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡
የአይዲ ፎር አፍሪካ – 2025 ጉባኤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ዛሬ ጠዋት የተከፈተ ሲሆን፥ ኢትዮጵያ ጉባኤውን በማስተናገዷ ኩራት ይሰማታል ሲል ጽ/ቤቱ ቤት ገልጿል፡፡
አይዲ ፎር አፍሪካ ማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ልማትን፣ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽንንና ሰብዓዊ ጥረቶችን የሚያበረታቱ ጠንካራና ኃላፊነት የሚሰማቸው የማንነት ዐውዶችን በመገንባት፣ የአፍሪካ ሀገራትን ለመደገፍ ቁርጠኛ የሆነ የፓን አፍሪካ እንቅስቃሴ መሆኑንም አመልክቷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በጉባኤው ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፥ ኢትዮጵያ ከተበታተነ የመታወቂያ ሥርዓት አልፋ፣ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ወደተጀመረው አስተማማኝ፣ ሁሉንም ያካተተ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ መሸጋገሯን አጽንዖት ሰጥተዋል።
90 ሚሊየን ሰዎችን ለመመዝገብ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ እስካሁን ከ15 ሚሊየን በላይ ሰዎች ለፋይዳ አገልግሎት መመዝገባቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡
ፋይዳ ሁሉም ዜጎች በተለይ ሴቶች፣ ወጣቶችና የተፈናቀሉ ማኅበረሰቦች አስፈላጊ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑንም አሳውቀዋል።
እንደ ፋይናንስ፣ ጤናና ትምህርት ባሉ ቁልፍ ዘርፎች የተቀናጀው ፋይዳ፣ 9 ነጥብ 6 ትሪሊየን ብር በዲጂታል ግብይት እንዲዘዋወር እያገዘ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
Exit mobile version