አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ አዳዲስ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ወደ ሥራ መግባታቸው በኮንስትራክሽን ዘርፍ ለተሰማሩ አልሚዎች ምቹ አጋጣሚ መፍጠሩን ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ገለጹ።
ፕሬዚዳንት ታዬ በድሬዳዋ ከተማ የተገነባውን የፓዮኔር ሲሚንቶ ማኑፋክቸሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ማስፋፊያ ፕሮጀክት መርቀዋል።
በዚሁ ወቅትም በኢትዮጵያ እና በቻይና ባለሃብቶች አጋርነት የተገነባው ፓዮኔር ሲሚንቶ ፋብሪካ ለኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ዕድገት ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ እና የዓለም አቀፍ አልሚ ባለሃብቶች አጋርነት የዕውቀት ሽግግርና የካፒታል ፍሰትን እንዲሁም ምርታማነትን ማረጋገጥ የሚያስችል ሁኔታ መኖሩን የሚያመላክት ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የኮንስትራክሽን ዘርፉ የሚያስፈልገውን ግብዓት ለማግኘት ጥልፍልፍ መንገዶችን ይጠይቅ እንደነበርም አውስተዋል፡፡
በኢትዮጵያ አዳዲስ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ወደ ሥራ መግባታቸው በኮንስትራክሽን ዘርፍ ለተሰማሩ አልሚዎች ምቹ አጋጣሚ እየፈጠረ እንደሚገኝ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በኮንስትራክሽን ዘርፍ ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት ሀገር የጀመረችውን የልማት ጉዞ ከማሳለጥ በላይ አዋጭ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
የፓዮኔር ሲሚንቶ ፋብሪካም በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በዕውቀት ልማትና ሽግግር ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑ ያስመሰግነዋል ነው ያሉት።