አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አመራር ዕጩ አቅራቢ ኮሚቴ የተመረጡ ዕጩዎችን ይፋ አደረገ፡፡
የኮሚቴው ሰብሳቢ ቀሲስ ታጋይ ታደለ የምልመላ ሂደቱን እና የተመረጡ ዕጩዎችን ይፋ ሲያደርጉ እንዳሉት፤ በቀረቡት ተወዳዳሪዎች ላይ የልየታ ሥራ ከተሠራ በኋላ የመጨረሻ ስድስት ዕጩዎች ተመርጠዋል፡፡
በዚህም መሠረት፤ 1ኛ. አቶ ተስፋዬ ንዋይ፣ 2ኛ. አቶ ተክሊት ይመስል፣ 3ኛ. ወ/ሮ ነሲ አሊ፣ 4ኛ. ወ/ሮ ዳሮ ጀማል 5ኛ. ወ/ሮ ፍሬህይወት ግርማ እና 6ኛ. ዶ/ር ያሬድ ሀብተ ማርያም በአዋጁ መሠረት መስፈርቱን በማሟላታቸው ሦስት የማጣሪያ ሂደቶችን አልፈው ተመርጠዋል ብለዋል፡፡
የተመረጡት ዕጩዎች፤ ተአማኒነት ያለው ምርጫ እንዲካሄድ እንደሚሠሩ እና ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባልነት ነጻ መሆናቸውን ቀሲስ ታጋይ ተናግረዋል፡፡
ኮሚቴው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መጋቢት 17 ቀን 2017 ዓ.ም ተቋቁሞ የቀረቡ ዕጩዎችን በአዋጁ መሠረት ለቀረቡ ክፍት ቦታዎች የመለየት ሥራ ሲሠራ መቀየቱ ተገልጿል፡፡
በሥራ ሂደትም፤ የብሔር እና የፆታ እኩልነት እንዲኖር እንዲሁም ሁሉንም አሳታፊ ለማድረግ መሠራቱ ተጠቅሷል፡፡
የተመረጡት ስድስት ዕጩዎች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚቀርቡ ሲሆን፤ እርሳቸው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበው ከስድስቱ የመጨረሻ ዕጩዎች ሦስቱ ጊዜያቸውን ባጠናቀቁ የምርጫ ቦርድ አባላት የሚተኩ ይሆናል።
በወንድማገኝ ጸጋዬ