አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የምርጫ ቦርድ አመራሮች መልማይ ኮሚቴ በዛሬው ዕለት ሪፓርቱን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ማቅረቡን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡
ኮሚቴው ለቦርዱ አመራርነት በቀረቡት ተወዳዳሪዎች ላይ የልየታ ሥራ በማከናወን በአዋጁ መሠረት መስፈርቱን በማሟላታቸው የተመረጡትን የመጨረሻ ስድስት ዕጩዎች ዛሬ ይፋ ማድረጉ ይታወቃል፡፡
በዚህም መሠረት 1ኛ አቶ ተስፋዬ ንዋይ፣ 2ኛ አቶ ተክሊት ይመስል፣ 3ኛ ወ/ሮ ነሲ አሊ፣ 4ኛ ወ/ሮ ዳሮ ጀማል 5ኛ ወ/ሮ ፍሬህይወት ግርማ እና 6ኛ ዶ/ር ያሬድ ሀብተ ማርያም ሦስት የማጣሪያ ሂደቶችን አልፈው መመረጣቸውን ኮሚቴው ገልጿል፡፡
የምርጫ ቦርድ አመራሮች መልማይ ኮሚቴ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መጋቢት 17 ቀን 2017 ዓ.ም መቋቋሙ ይታወሳል፡፡