Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በመፈረሙ የሚቆጫቸው አንዳንድ አካላት ግጭት እንዲፈጠር ፍላጎት አላቸው – የፕሪቶሪያ ዋና ተደራዳሪዎች

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በመፈረሙና የሰው ህይወት በመትረፉ የሚቆጫቸው አንዳንድ አካላት አሁንም ግጭት እንዲፈጠር ፍላጎት እንዳላቸው የፕሪቶሪያ የሰላም ንግግር ዋና ተደራዳሪዎች ገለጹ።

የፕሪቶሪያ የሰላም ንግግር ዋና ተደራዳሪዎች የነበሩት የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀኔራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ነው ይህንን የገለጹት።

በቆይታቸውም÷ የሰሜኑ ግጭት ከተከሰተ በኋላ ከፌደራል መንግስቱ ጋር የሰላም ንግግሮች እየተደረጉ ባሉበት ወቅት ስምምነት እንዳይደረስ እንዲሁም ግጭትና መከፋፈል እንዲቀጥል የሚፈልግ ጥቂት የቀድሞ ህወሓት ቡድን ነበር ብለዋል።

አቶ ጌታቸው ረዳ ይህ ቡድን የራሱን የስልጣንና የሀብት ጥቅም ከማጋበስ ያለፈ አላማ እንደሌለው በመግለፅ የትግራይን ህዝብ እንደማይወክልም አንስተዋል።

በግጭቱ ወቅት እኛ ኢትዮጵያ ትውደም እያልን እንኳ በትግራይ አብያተ ክርስቲያናት ጭምር ኢትዮጵያዊነት ይሰበክ ነበር ብለዋል።

የትግራይ ህዝብ ኢትዮጵያዊነቱን አጽንቶ የኖረ ነው ያሉት አቶ ጌታቸው÷ ለዘመናት ኢትዮጵያ ጠል ኃይሎች ሲነዛ በኖረ የመነጠል ትርክት ሳይደናገር ስለ ኢትዮጵያ የጸና አቋሙን በተግባር ማሳየቱንም አንስተዋል።

በግጭቱ ወቅት ህዝቡ ኢትዮጵያን እንዲጠላ ለማድረግ በተሰራጩ የተዛቡ ትርክቶች መጥፎ ስሜቶች መፈጠራቸውን አንስተው÷ ህዝቡ ችግር ሲፈጠርም የሚመጣው ወደ አስመራ ሳይሆን ወደ አዲስ አበባ ነው ብለዋል።

አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በበኩላቸው÷ አንዳንድ አካላት የግልና የንዑስ ቡድን ኩርፊያቸውን የመነጠል ትርክትን በማቀንቀን ለማሳየት ይሞክራሉ ብለዋል።

ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ግጭትን በማራዘም የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አፈጻጸም እንዲደናቀፍ ተደጋጋሚ ሙከራ እንደሚያደርጉ በማንሳት፥ ሆኖም ጸብም ካለ ከኢትዮጵያ ጋር ሳይሆን ከአስተዳደር ጋር መሆን ነበረበት ነው ያሉት።

የትግራይ ህዝብ የመነጠል ትርክት በሚያቀነቅኑ አካላት ቅንጣት ታክል የመደናገር ስሜት እንደሌለው ገልጸው÷ በኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍ ውስጥ ዘላቂ ሰላም የማረጋገጥና በጋራ የመልማት ፍላጎት ነው ያለው ብለዋል።

በግጭቱ የተፈጠሩ መጥፎ ስሜቶችን በማረቅ የጋራ እጣፈንታን በአንድነት ለማሳካትም የወል ትርክትን መገንባት እንደሚገባ ገልጸዋል።

ተደራዳሪዎቹ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በመፈረሙና የሰው ህይወት በመትረፉ የሚቆጫቸው አንዳንድ አካላት አሁንም ግጭት እንዲፈጠር ፍላጎት አላቸው ብለዋል።

ለአብነትም ላለፉት ሁለት ዓመታት ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ የፌደራል መንግስት የጀመራቸውን ሂደቶች እያደናቀፉ በቁስላቸው እየነገዱባቸው መሆኑንም ተናግረዋል።

የፌደራል መንግሥቱ በክልሉ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነትን በማስፈጸም ረገድ በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን ጠቅሰው ተፈናቃዮችን የመመለስ ስራ ተጀምሮ ነበር ብለዋል።

ሆኖም ተፈናቃዮች ወደቀያቸው እንዳይመለሱና በድንኳን እንዲሰቃዩ እያደረገ በቁስላቸው የሚነግደው ኃይል ሂደቱን እያደናቀፈ ነው ብለዋል።

ይህ ኃይል የተፈናቃዮች መመለስና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ስራውን በአግባቡ መስራት ጥቅሙን ስለሚያስቀርበት አሁንም ችግር እየፈጠረ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

Exit mobile version