Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር) የፈረንሳይ ጉብኝት የዕውቀት ልውውጦችን አስፈላጊነት ያሳየ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በፈረንሳይ ፓሪስ ያደረጉት የኢንዱስትሪ ጉብኝት በቴክኖሎጂ እና የአርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ላይ ማተከሩ ተገልጿል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከልዑካቸው ጋር በመሆን ‘ስቴሽን ኤፍ’ የተሰኘውን በዓለም ትልቁን የግል የቴክኖሎጂ የስታርት አፕ የቢዝነስ መፍጠሪያ ማዕከል መጎብኘታውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ስታርት አፕ ከባቢ ገና በጅምር ደረጃ ያለ ቢሆንም፤ የቴክኖሎጂ ዕውቀት ጠገብ በሆኑ ወጣቶች የተሞላ እንዲሁም ጠንካራ አቅም እያሳየ በማደግ ላይ ባለ የዲጂታል ትስስር እየተመራ የሚገኝ መሆኑን ጽሕፈት ቤቱ ጠቁሟል፡፡

መንግሥት እንደ “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025” ያሉ ስትራቴጂዎችን በመንደፍ ፈጠራን ለመደገፍ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ እንደሚገኝም ነው የገለጸው፡፡

ይህም ለስታርት አፕ ከባቢ በተለይም በፋይናንስ ቴክኖሎጂ፣ በግብርና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በኢ-ኮሜርስ ግብይት አስቻይ ሁኔታን ለመፍጠር ያለመ ነው ተብሏል፡፡

በተጨማሪም የ’ስታርት አፕ’ አዋጅ የተሰኘ ሁሉን አቀፍ አዋጅ በማውጣት ለስታርት አፕ እንቅስቃሴዎች የህግ እና ተቋማዊ ማዕቀፎችን በማበጀት ውስን የሆነውን የገንዘብ አቅርቦት የሚያሰፋ፣ የቁጥጥር ተግዳሮቶችን እና መሰል ፈተናዎችን ለማለፍ የሚያስችል ሁኔታ ፈጥሯል ነው የተባለው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ5G እና 6G ቴክኖሎጂ፣ በሳይበር ደኅንነት፣ በአርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ እና የኦፕቲካል ትስስር ማዕከል የሆነውን የኖኪያ-ፈረንሳይ ዋና መሥሪያ ቤትን መጎብኘታቸውም ተጠቅሷል፡፡

እንደ ጽሕፈት ቤቱ መረጃ፤ ጉብኝቱ የፋይበር ሴንሲንግ (fiber sensing) አቅርቦት፣ የኃይል ቁጠባ ብልሃት እና የ5G ላቦራቶሪዎች ምልከታን ያካተተ ነው፡፡

ይህም በዘርፉ ፈጠራ፣ መሠረተ ልማት ግንባታ እና ዘርፍ ዘለል ትብብሮች ላይ ለኢትዮጵያ ዋጋ ያላቸው ትምህርቶች የተገኙበት ነበር ተብሏል፡፡

በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፈረንሳይ የሚገኘውን ታሌ የምርምር እና የቴክኖሎጂ ማዕከልን ጎብኝተዋል፡፡

ይህ በብዝሃ ዘርፍ የሚንቀሳቀስ የታሌ ግሩፕ የምርምር ተቋም ዓለም አቀፍ የምርምር ጥረት የማዕዘን ድንጋይ ሆኖ የሚያገለግል ማዕከል ሲሆን፤ በኤሮስፔስ፣ መከላከያ እና አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ መስኮች ላይ ማጠኮሩ ተገልጿል፡፡

ጉብኝቶቹ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነቶቹ፤ የኢትዮጵያን የዲጂታል ሽግግር በማፋጠን የአፍሪካ የፈጠራ እና የቴክኖሎጂ ማዕከል እንድትሆን በማመቻቸት ረገድ የዕውቀት ልውውጦችን አስፈላጊነት የሚያሳዩ ናቸው ነው የተባለው፡፡

Exit mobile version