አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጣሊያን ያደረጉት ይፋዊ ጉብኝት የሀገራቱን ግንኙነት ለማጠናከር ስምምነት ላይ የተደረሰበት ስኬታማ ቆይታ እንደነበር የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጣሊያን አቻቸው ጂኦርጂያ ሜሎኒ ጋር ያደረጉትን ውይይት በተመለከተ የገንዘብ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በሁለቱ ሀገራት መሪዎች መካከል ያለው ወዳጅነት የሀገራቱን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር ያስቻለ መሆኑን አቶ አሕመድ ሺዴ አንስተዋል፡፡
ጣሊያን ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገትና ሪፎርም እንዲሁም ለኢነርጂ ዘርፍ ልማት በፋይናንስ ጭምር እያደረገች ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን አንስተዋል፡፡
ለአብነትም ባለፉት ጥቂት ዓመታት የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ልማት፣ የከተማ ልማትና የኢነርጂ ዘርፍን ጨምሮ ለተለያዩ ዘርፎች ድጋፍ የሚውል ከ260 ሚሊየን ዩሮ በላይ የልማት ስምምነቶች መፈረማቸውን ጠቁመዋል፡፡
በሁለቱ መሪዎች መካከል በተደረገው ውይይት ላይ የጣሊያን መንግስት ኢትዮጵያ እያካሄደችው ላለው የኢኮኖሚ ሪፎርም የሚያደርገውን ድጋፍ ይበልጥ አጠናክሮ እንዲቀጥል ስምምነት ላይ የተደረሰበት መሆኑንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ጂኦርጂያ ሜሎኒ የጣሊያን ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ የፈጠረውን ምቹ የኢንቨስትመንት እድል እንዲጠቀሙ እንደሚያበረታቱ አረጋግጠዋል፡፡
በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ብፁዕ ወቅዱስ ፖፕ ሊዮ 14ኛ ጋር በተለይም በሰላምና በትምህርት ልማት ዙሪያ መወያየታቸውን አቶ አሕመድ ሺዴ ገልጸዋል፡፡
በውይይታቸውም በሁለትዮሽና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ በመምከር ትብብራቸውን አጠናክረው ለማስቀጠል መስማማታቸውንም ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡
በተመሳሳይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዊቢዩልድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፔይትሮ ሳሊኒ ጋር ባደረጉት ውይይት ኩባንያው በኢትዮጵያ እያከናወናቸው ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን አጠናክሮ እንዲቀጥል ማሳሰባቸውን ነው ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው የገለጹት፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ