አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ ተረጂነት የሚፈልጉ የሕብረተሰብ ክፍሎች 86 በመቶ እንዲቀንስ ማድረጉን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለ ማርያም (ዶ/ር) እንደገለፁት፤ በ2018 ዓ.ም በሀገሪቱ ለሚከሰቱ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ አደጋዎች በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት እየተሠራ ነው፡፡
እንደ ሀገር ለተፋጥሯዊና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ምላሽ ለመስጠት 500 ሺህ ሜትሪክ ቶን መጠባበቂያ የእህል ክምችት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡
እንዲሁም ኮሚሽኑ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል የዕለት ደራሽ ምግብ ክምችት እንዲኖር እየሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በመኸር ከሚሰበሰበው ምርትም 20 ሚሊየን ኩንታል የአደጋ ጊዜ መጠባበቂያ እህል ወደ መጋዘን ይገባል ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል በቀጣይ እንደሚፀድቅ የሚጠበቀው የአደጋ ጊዜ ምላሽ ፈንድ ፖሊሲ በአደጋ ወቅት ምላሾችን በራስ አቅም ለመመለስ የሚደረገውን ጥረት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያግዝ ገልጸዋል፡፡
በእዮናዳብ አንዱዓለም