አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የምታደርገውን ሰላማዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ጥረት የአሜሪካ መንግስት ይደግፋል አሉ፡፡
ኢትዮጵያ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት እያስመዘገበች መሆኗን ገልጸው÷ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሰላም እና ፀጥታ ለማረጋገጥ አሜሪካ ከወሳኝ አጋሯ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ እንደምትሰራ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ መንገድ የባህር በር ለማግኘት እንደምትሰራ በአጽንኦት መግለጻቸው ይታወሳል።
አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ኢትዮጵያ ሰፊ የህዝብ ቁጥር ያላት እና ፈጣን ኢኮኖሚ እያስመዘገበች እንደምትገኝ አንስተው÷ ይህ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት እንደሚቀጥልም ትንበያ መኖሩን አመልክተዋል።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በዓለም ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ ለመገንባት ያላትን ህልም ለማሳካት የባህር በር አማራጯን ማስፋት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው÷ በሰላማዊ እና ዲፕሎማሲያዊ መንገድ የባህር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት የአሜሪካ መንግስት የሚደግፈው መሆኑን አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ ቀጣናው ወደ መረጋጋትና ሰላም እንዲመለስ አስተዋጽኦ እያደረገች መሆኑን አመልክተው÷ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ መስራት አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ ያላት ጠንካራ አቋም መሆኑን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣናው ግዙፍ ብቻ ሳትሆን አቅም እና ተጽዕኖ ያላት ሀገር ነች ያሉት አምባሳደር ማሲንጋ÷ በቀጣናው መረጋጋትና ሰላም ለማስፈን ሀገራቱ በጋራ እንደሚሰሩም መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።