አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) 1 ሺህ 446ኛው የዒድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓል መከበር ጀምሯል።
በዓሉ በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በመላ ሀገሪቱ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓቶች ነው እየተከበረ የሚገኘው፡፡
በበዓሉ አከባበር ሰላት እና ተክቢራን ጨምሮ የተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓቶች በመከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ሕዝበ ሙስሊሙ የአረፋ በዓልን ሲያከብር የእምነቱን አስተምሮ በመከተልና በመተግበር ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።
ነቢዩ መሐመድ በአስተምሯቸው የአረፋ ቀን ከሁሉ የላቀች ናት ማለታቸውን አውስተው÷ በአረፋ ተራሮች መቆም ያልቻልን አማኞች ባለንበት ዱዓ በማድረግ መልካሙን በመመኘት ጭምር ልናሳልፍ ይገባል ብለዋል።
በመሆኑም በዓሉን በአንድነት፣ በመረዳዳት እና የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ ማክበር እንደሚገባ አሳስበዋል።