አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) መንግሥት በዓላት የብዝኃነት እና የአብሮነት ማሳያ እንዲሆኑ አስፈላጊውን እንክብካቤ እና ጥበቃ ያደርጋል አለ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፡፡
አገልግሎቱ ለእስልምና ሐይማኖት ተከታዮች ለዒድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል የእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት አስተላልፏል፡፡
በመልዕክቱም፤ ሐይማኖታዊ እና ሕዝባዊ በዓላት የብዝኃነት ማሳያ የአብሮነታችን ምሳሌ ናቸው ብሏል።
ኢትዮጵያ ሐይማኖታዊ እና ሕዝባዊ በዓላት የብዝኃነት ማሳያ እና የአብሮነት ምሳሌ የሆኑባት ሀገር መሆኗንም አስገንዝቧል፡፡
በዓላቱ ሐይማኖታዊ፣ ባህላዊ፣ ብሔራዊ፣ የቤት ውስጥ ወይም የዐደባባይ ሊሆኑ ይችላሉ ነው ያለው።
መሠረተ ሐሳባቸው ግን ደስታን፣ ተስፋን፣ ብሔራዊነትን መጋራት እና መተጋገዝ መሆኑን አስረድቷል፡፡
ዛሬ በእስልምና ሐይማኖት ተከታዮች ዘንድ እየተከበረ የሚገኘው የዒድ አል-አድሃ በዓል መረዳዳት፣ መተሳሰብና አንድነት ጎልቶ ከሚንጸባረቅባቸዉ በዓላት መካከል አንዱ ነው ብሏ አገልግሎቱ።
በዚህ በዓል ያለው ለሌለው ማዕድ የሚያጋራበት፣ አብሮነትና ወዳጅነት የሚያጠናክርበት ስለመሆኑም ገልጿል፡፡
ብዝኃነትን ጌጥ፣ መረዳዳትንና ማዕድ ማጋራትን ባህል እያደረገ የመጣው የለውጡ መንግሥትም፤ እነዚህ በዓላት የብዝኃነት እና የአብሮነት ማሳያ እንዲሆኑ አስፈላጊውን እንክብካቤ እና ጥበቃ ያደርጋል ነው ያለው፡፡
ዜጎች ሐይማኖታዊ እና ሕዝባዊ በዓላትን በድምቀት እና በአብሮነት እንዲያከብሩ መንግሥት አበክሮ እንደሚሠራም ነው ያረጋገጠው፡፡