Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በኢትዮጵያ ውስጥ ሃሳቡን ስለገለጸ የሚታሰር ሰው የለም – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አሁን ላይ በኢትዮጵያ የስልጣን ፍላጎትን በሃይል ለመያዝ እቅድ አውጥቶና ተደራጅቶ ሲንቀሳቀስ እንዲሁም በሌሎች ወንጀሎች ላይ ሲሳተፍ እንጂ ሃሳቡን ስለገለጸ የሚታሰር ሰው የለም አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአራተኛው ክፍል እና በመጨረሻው ቃለ ምልልሳቸው በኢትዮጵያ የዜጎችን የሰብዓዊ መብት በማስጠበቅ ረገድ የተሰሩ ሥራዎችን አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በዚህም መንግስት ከየትኛውም ጊዜ በተሻለ መልኩ ለዜጎች ሰብዓዊ መብት መከበር ቁርጠኛ አቋም ይዞ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ትልቁ ችግር ነጻነትን የማስተዳደር አቅም ውስን መሆን ነው፤ ነጻነትን በተገቢው ማስተዳደር ፈተና ሆኗል ነው ያሉት፡፡

የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን ሁሉም በትክክል አውቆና ተረድቶ በተቋም አቅም ተፈትሸው እንዲተገበሩ መሰራቱን አስረድተዋል፡፡

ለአለብነትም በነጻነት የሚሰሩ ተቋማት መገንባታቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ለሰብዓዊ መብት መከበር  ዋጋ እየተከፈለም ቢሆን አስፈላጊው ምህዳር መመቻቸቱን አንስተዋል፡

በወንጀል የሚሳተፉ ሰዎች በተለይም ፖለቲከኛ ነን እና አክቲቪስት ነን የሚሉ ሰዎች በወንጀል ተሳትፈው በሕግ አግባብ ሲጠየቁ የሰብዓዊ መብት ጥያቄ ያነሳሉ፤ ይህም ስህተት ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ሃሳቡን ስለገለጸ የሚታሰር ሰው እንደሌለ አስገንዝበው÷ ሰው የሚታሰረው እቅድ አውጥቶ ተደራጅቶ፣ ፋይናንስ ፈልጎና ተንቀሳቅሶ አራት ኪሎ እገባለሁ ሲል ነው ብለዋል ፡፡

ስልጣንንና ፍላጎትን በሃይል ለማሳካት ሙያን መደበቂያ ካባ ማድረግ እንዲሁም ሕገ መንግስት እና ሌሎች ሕጎችን አክብሮ የማይንቀሳቀስ አካል በሕግ ተጠያቂ ከመሆን አያመልጥም ነው ያሉት፡፡

ይህ ማለት ሕግ በማስከበር ሒደት ላይ እንከኖች የሉም ማለት አይደለም፤ በቀጣይ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማስተካከል በትኩረት እንደሚሰራ አንስተዋል፡፡

ሰብዓዊ መብት ማለት ሕግ በማክበር፣ ግዴታን በመወጣት መብትን በመጠየቅ ብቻ የሚከበር መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባ አረድተዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

Exit mobile version