አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የሳይንስ ሙዚየም ቋሚ ኤግዚቢሽን ክፍል በይፋ ተከፍቷል፡፡
በአርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና የኢትዮጵያ ምላሽ፣ ግብርና፣ የውኃ ኃይል እና ኢነርጂ፣ ኤሮኖቲክስ እና አቪየሽን ላይ ያተኮሩ አምስት የዐውደ ርዕይ ምድቦችን የያዘ ነው።
ይህም ሀገራችን ሳይንስ እና ቴክኖሎጂን ለመጠቀም ያላትን ጽኑ ፍላጎት የሚያሳይ ስለመሆኑ ተመላክቷል፡፡
በተጨማሪም በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው የህዋ ቅርጽ ሉላዊ የትዕይንት አዳራሽም ይፋ ሆኗል።
በ1 ሺህ ሜትር ስኩዌር ሜትር እና 36 ሜትር ዲያሜትር ይዞ ያረፈው አዳራሽ ዘመኑን በዋጀ የ4k ዲጂታል ምስል ማሳያ ቴክኖሎጂ የተገጠመለት ሲሆን ምስለ-ህዋው ከፍተኛ ጥራት ያለው እጅግ አስደማሚ ምስሎችን በማቅረብ የህዋውን አለም እጅግ አቅርቦ እንደሚያሳይም ተጠቁሟል፡፡
እውቀት ለማሰስ፣ ለመማር እና ለመነሳሳት ምቹ የሆነው የሳይንስ ሙዚየም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በዛሬው ዕለት ለጎብኝዎች ክፍት ሆኗል።