Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ከሕገ መንግስቱ መታረቅ እና መስተካከል ያለበትን ጉዳይ ለማስተካከል ዝግጁ ነን – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዋና እና ወሳኝ ጉዳዮች ሕገ መንግስቱ መታረቅ፣ መስተካከል ያለበትን ጉዳይ ለማስተካከል ዝግጁዎች ነን አሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመላው ኢትዮጵያ ከተወጣጡ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት እንዳሉት፥ ሕገ መንግስት መቀየር የመንግስት ስራ ብቻ አድርጎ የመውሰድ ችግር አለ።

ይሄ መንግስት በሕገ መንግስት የተፈጠረ እንጂ ሕገ መንግስት ፈጣሪ፣ ቀዳጅ እና አጥፊ እንዳልሆነ አንስተው፥ መሰል ሃሳብ እንደማያዋጣ አስረድተዋል።

መንግስት በሕገ መንግስቱ ጥላ ስር የተፈጠረ አንድ አካል፤ በለውጡ ውስጥ ደግሞ አንድ ተዋኝ መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ብቻውን መቅደድ እና መቀየር የሚችል ከሆነ ከትላንቱ የተለየ አይሆንም፤ እኛም ይሄንን አንደግፍም ነው ያሉት።

እኛ የምንፈልገው በውይይት፣ በንግግር፣ በምክክር ፤ለለውጥ ለልማትና ለአንድነት የሚጠቅሙ ጉዳዮችን ቅድሚያ በመስጠት በጊዜ እያስተካከልን እና እያረምን መሄድ ነው ሲሉ አስገንዝበዋል።

በአንጻሩ ቀዶ እንደገና መጻፍ ይቻላል፤ ነገር ግን ይህ የምናስባት ኢትዮጵያን አይፈጥርልንም ብለዋል።

ከእናንተ ጋር አንድ አካል ሆነን በዋና እና ወሳኝ ጉዳዮች ሕገ መንግስቱ መታረቅ፣ መስተካከል ያለበትን ጉዳይ ለማስተካከል ዝግጁ ነን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ለዚህም አካታች ሀገራዊ ምክክር እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል።

እንደማንኛውም ቀደምት የኢትዮጵያ መንግስትና አሁን እንዳሉት የአፍሪካ መንግስታት፤ ሕገ መንግስቱን መቀየር የሚያስችል ስልጣን ቢኖረንም ትክክል ነው ብለን አናምንም፤ ስለሆነም ጉዳዩን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመወያየት ጊዜ ሰጥቶ መፈተሽ እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል።

በዮናስ ጌትነት

Exit mobile version