Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያና አሜሪካ በሠላምና ጸጥታ ያላቸውን ትብብር አጠናክረው ይቀጥላሉ – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያና አሜሪካ በሠላምና ጸጥታ ጉዳይ ያላቸውን ሁለንተናዊ ትብብር አጠናክረው ይቀጥላሉ አሉ የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፡፡

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የአሜሪካ በአፍሪካ ዕዝ አዛዥ (አፍሪኮም) ጀነራል ሚካሄል ላንግሌይ የተመራ ልዑክን ተቀብለው አነጋግረዋል።

ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ በዚህ ወቅት ÷ አሜሪካና ኢትዮጵያ ከ100 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳላቸው አስታውሰዋል፡፡

ሁለቱ ወዳጅ ሀገራት በቀጣይ በመከላከያ ዘርፉ በትብብር ለመስራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መግባባት መድረሳቸውን ተናግረዋል፡፡

በቀጣናው ባለው ሁኔታ የጋራ መግባባት የተያዘበትና በተለይም በቀይ ባሕር እና በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በሚታዩ የጸጥታ ጉዳዮች ላይ ለጋራ ተጠቃሚነት በትብብር ለመስራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይም ተስማምተዋል፡፡

ጀነራል ሚካኤል ላንግለይ በበኩላቸው ÷ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድና በቀጣናው ከፍተኛ ሚና ያላት ሀገር መሆኗን አውስተዋል፡፡

በተለይም በሶማሊያ ሰላምን ለማስፈን እና ሽብርተኝነትን ለመዋጋት እያደረገች ላለው ጥረት ያላቸውን አድናቆት ገልፀዋል።

በውይይታቸው በቀጣናው ያለውን ሁኔታ በግልጽ እንደተረዱ ጠቁመው÷በቀጣይ በወታደራዊና ጸጥታ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን ተናግረዋል።

በውይይቱ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋን ጨምሮ ከፍተኛ የኢትዮጵያና የአሜሪካ ወታደራዊ አመራሮች መገኘታቸውን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡

በመላኩ ገድፍ

Exit mobile version