Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮጵያን የጋራ ራዕይ ለመገንባት የሚተጋ ሚዲያ ያስፈልጋል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያን የጋራ ራዕይ ለመገንባት የሚተጋና የጋራ አስተሳሰብ እንድንይዝ የሚያደርግ ሚዲያ ያስፈልጋል አሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሕዝብ እና የግል ሚዲያ ባለሙያዎች ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት፥ ሚዲያን በአግባቡ ተገንዝበን መጠቀም ካልቻልን ጥፋትም ልማትም ሊያስከትል እንደሚችል ማወቅ ይገባል፡፡

ጥፋት እንዳያስከትል ለሀገር ግንባታ፣ ለሰላም እና ለልማት መርህ ያለው ሚዲያ እንዲኖረን አድርገን ከቀረፅነው ዋነኛውን የሚዲያ ተልዕኮ እንደሚፈፅም ገልጸዋል፡፡

የሚዲያ ዋነኛ ተልዕኮ ማህበረሰባዊ ንቃት መፍጠር መሆኑን ገልፀው፥ የነቃ ማህበረሰብ ብሄራዊ ጥቅሙን፣ ዓለምን እና ራሱን በሚገባ ያውቃል ነው ያሉት፡፡

የጋራ ራዕይ ለመገንባት የሚተጋና የጋራ የሆነ አስተሳሰብ እንድንይዝ የሚያደርግ ሚዲያ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ላንተገነቡ ሀገራት በእጅጉ እንደሚያግዝ ጠቁመው፥ ደመወዝ ሲከፈለን ብቻ ሳይሆን በአቋሙ የሚፀና የሚዲያ ባለሙያ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ጋዜጠኝነትን በደንብ ሳናውቀው እና ብሄራዊ ጥቅምን ሳንረዳ ሚዲያውን የንግድ መሳሪያ ማድረግ ተገቢ አይደለም በማለትም አስገንዝበዋል፡፡

ኢትዮጵያ ያልተሰራችና የምትገነባ ሀገር ናት፤ ይህንን ለማድረግ በምንሄድበት ሂደት ላይ ሚዲያው አብሮን ሊሰራ ይገባልም ነው ያሉት፡፡

ጋዜጠኝነት እና ሚዲያው የኢትዮጵያን ፍላጎት አውቆ ብሄራዊ ጥቅምን በማስቀደም ስራዎችን መስራት እንዳለበት የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ(ዶ/ር)፥ ሚዲያዎች ከልመናና ከተረጂነት ወጥተው መስራት እንዲችሉ ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል፡፡

በወንድማገኝ ፀጋዬ

Exit mobile version