Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የዛሬ ስኬታችሁ የሚለካው ለኢትዮጵያ በምታደርጉት አስተዋፅኦ ነው – ፕሬዚዳንት ታዬ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ የዛሬ ስኬታችሁ የሚለካው ለኢትዮጵያ እና ለህዝቦቿ በምታደርጉት አስተዋፅኦ ነው አሉ፡፡

የአልማዝ ኢዮቤልዩ በዓሉን እያከበረ የሚገኘው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በዛሬው ዕለት 3 ሺህ 334 የመጀመሪያ ዲግሪ፣ 2 ሺህ 859 የሁለተኛ ዲግሪ፣ 304 የሦስተኛ ዲግሪ እና 352 የስፔሻሊቲ እና ሰብ-ስፔሻሊቲ በአጠቃላይ 6 ሺህ 849 ተማሪዎችን አስመርቋል።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለ75 ዓመታት ሲመራመር ሲያስተምር የኢትዮጵያ አዕምሮ ሆኖ ቆይቷል ሲሉ የዩኒቨርሲቲውን የዓመታት ሥራ አስታውሰዋል።

የዓለምን ፖለቲካ መርምሩ ይህንን ስታደርጉ ሀገራችሁ ኢትዮጵያን ቀዳሚ ማድረግ ትችላላችሁ ብለዋል፡፡

ተመርቃችሁ ወደ ህዝቡ ስትቀላቀሉ የምትቀላቀሉት ዓለም ተለዋዋጭ ጂኦ ፖለቲካ እና ጂኦ ኢኮኖሚክ በመሆኑ ይህንን በመረዳት ተስፋ ሳትቆርጡ ሀገራችሁን ለማገልገል ዝግጁ ልትሆኑ ይገባል ነው ያሉት፡፡

ዓለም አቀፍ ችግሮች በመበራከታቸው ተስፋ ሳትቆርጡ የኢትዮጵያን ፍጎላት እና ብሔራዊ ጥቅም በማስቀደም ልትሰሩ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የዛሬ ስኬታችሁ የሚለካው ለኢትዮጵያ እና ለህዝቦቿ በምታደርጉት አስተዋፅኦ ነው ብለዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ታዬ ሁሉን መርምሩ መልካሙን ግን ያዙ ሲሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዋና ግቢ የሚገኘውን የዘመናት መልዕክት በማንሳት ለተመራቂዎች የአደራ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ መልክ የሆነ በሀገራችን የከፍተኛ ትምህርት ጅማሮ ማብሰሪያ የሆነ ተቋም ነው ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው የልህቀት ማዕከልነቱን ለማስጠበቅና ለማላቅ የተማሪዎችን ስኬት የሚያግዙ እና የመምህራንን ብቃት ከፍ የሚያደርጉ እርምጃዎች በመውሰድ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው የጀመረው የራስ ገዝ አስተዳደር የአካዳሚ ነፃነቱን የመለሰለት መሆኑን አንስተው፤ የተለያዩ ምርምሮችን በማድረግ እና የጥናት ጽሁፎችን በማዘጋጀት የልህቀት ማዕከልነቱን አጠናክሮ እያስቀጠለ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ዩኒቨርሲቲውን ዲጂታል ለማድረግ በሚደረገው ጥረትም ስድስት ኪሎ የሚገኘውን ዋና ግቢ ስማርት የማድረግ እና የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልንም የዲጂታል ህክምና አገልግሎት እንዲሰጥ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

በዘመን በየነ
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

Exit mobile version