Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በክልሉ በቀጣይ በጀት ዓመት ከ18 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ይሰራል – ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በ2018 በጀት ዓመት ገቢውን 80 በመቶ በማሳደግ ከ18 ቢሊየን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዷል አሉ ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)።

የክልሉ ገቢዎች ቢሮ የ2018 በጀት ዓመት የደረጃ ‘ሐ’፣ ‘ለ’ እና ‘ሀ’ ግብር ከፋዮች የግብር ማስጀመሪያ ንቅናቄ መድረክ አካሂዷል።

በመድረኩ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በ2017 በጀት ዓመት ለመሰብሰብ ከታቀደው 10 ቢሊየን ብር ውስጥ በ11 ወራት ከ9 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን አንስተዋል።

በ2018 በጀት ዓመት የክልሉን የገቢ አቅም አሟጦ በመጠቀም ከተለያዩ ዘርፎች የሚሰበሰበውን ገቢ 80 በመቶ ለማሳደግ እቅድ መያዙንና ከ18 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ እንደሚሰበሰብ ተናግረዋል።

የተያዘውን እቅድ ለማሳካት የገበያውን አቅም መሰረት ያደረገ የገቢ አሰባሰብ ስርዓትን በመከተል እንደሚሰራ ገልጸው÷ በዘርፉ ላይ ያሉ ማነቆዎችን ለመፍታት ቅድሚያ እንደሚሰጥ አመልክተዋል።

በተለይም የታክስ ማዕከላትን በቴክኖሎጂ በማስተሳሰርና በማዋቀር ፈጻሚዎች ላይ ያሉ የስነምግባር ብልሽቶችን ፈትሾ የግብር አሰባሰብና አስተዳደር ስርዓትን ማጠናከር ላይ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ህይወት አሰግድ በበኩላቸው÷ ክልሉ ሲመሰረት ከነበረበት 36 በመቶ የገቢ ድርሻ በ2017 በጀት ዓመት 57 በመቶ በላይ ማድረስ መቻሉን ጠቁመዋል።

በክልሉ ዘመናዊ የታክስ አስተዳደር ስርዓት በመገንባት የገቢ አሰባሰብ ሂደቱ የግብር ከፋዩን እንግልት በሚቀንስ አኳኋን እንዲፈፀም አስፈላጊው የዝግጅት ስራዎች መጠናቀቃቸውን አብራርተዋል።

በቅድስት በርታ

Exit mobile version