Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 48ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ምክር ቤቱ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች ዝርዝር እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው የኢትዮጵያ መንግስት ከዓለም ዐቀፍ የልማት ማህበር ጋር ለሁለተኛው ዘላቂ እና ሁሉን አቀፍ የእድገት ልማት ፖሊሲ ማስፈፀሚያ የሚውል 258,100,000 ኤስ.ዲ.አር እና ለፍጥነት መንገድ ልማት ድጋፍ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚውል 27,300,000.00 ኤስ.ዲ.አር የፋይናንስ ድጋፍ እና የብድር ስምምነቶችን ለማጽደቅ በቀረቡ ሁለት ረቂቅ አዋጆች ላይ ነው፡፡

ሁለቱም ብድሮች ከወለድ ነጻ፣ 0.75% የአገልግሎት ክፍያ የሚከፈልባቸው ሆኖ የ6 ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በረጅም ጊዜ የሚከፈሉ ናቸው፡፡
ምክር ቤቱም የብድር ስምምነቶቹ ከአገራችን የብድር አስተዳደር ስትራቴጂ ጋር የሚጣጣሙ መሆናቸውን በማረጋገጥ በሙሉ ድምጽ አጽድቆ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ ወስኗል፡፡
በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው የፌዴራል የገቢ ግብር አዋጅን ለማሻሻል የወጣ አዋጅ ላይ ነው፡፡
ቀደም ሲል ሲሰራበት የነበረው የፌዴራል የገቢ ግብር አዋጅ አሁን ከምንገኝበት ሀገራዊ እና አለም አቀፋዊ የኢኮኖሚ ሁኔታ አንጻር ሲታይ በርካታ ክፍተቶች ያሉበት በመሆኑ የአዋጁን ድንጋጌዎች በማሻሻል የታክስ ስርአቱ መሠረታዊ የታክስ መርሆዎችን ለማሳካት በሚያስችል መልኩ እንዲቀረጽ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የማሻሻያ አዋጁ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡
ምክር ቤቱም በማሻሻያ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ በሙሉ ድምጽ አጽድቆ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል፡፡
በመጨረሻም ምክር ቤቱ የተወያየው ከናይጄሪያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ መንግስት ጋር የዲፕሎማቲክ እና የሰርቪስ ፓስፖርት ለያዙ ሰዎች ቪዛን ለማስቀረት በተፈረመው የሁለትዮሽ ስምምነት ላይ ነው፡፡
ስምምነቱ የዲፕሎማቲክ እና የሰርቪስ ፓስፖርት የያዙ የሁለቱ አገራት ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ ዲፕሎማቶች እና ዜጎች ለሥራ ጉዳይ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ቪዛ ለማግኘት የሚያስፈልጉትን ቅድመ ሁኔታዎችና የሚወስደውን ጊዜ በማስቀረት እንዲሁም የሁለትዮሽ ግንኙነቱን በማጠናከር ረገድ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው በመታመኑ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡
ምክር ቤቱም በስምምነቱ ላይ ከተወያየ በኋላ በሙሉ ድምጽ አጽድቆ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል፡፡
Exit mobile version