አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ፍልሰት በአግባቡ ከተመራ የማደግና የልማት ዕድልን ይፈጥራል አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ፡፡
ብሔራዊ የፍልሰት ዓመታዊ ስብሰባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሬ በተገኙበት በዛሬው ዕለት ተካሂዷል፡፡
አቶ ተመስገን ጥሩነህ በዚሁ ወቅት፥ የሀገራችንን ሉዓላዊነት፣ ደህንነትና የመልማት ፍላጎት ከፍልሰተኞች ሰብዓዊ መብትና ክብር ጋር አመዛዝኖ መምራትን ይጠይቃል ብለዋል፡፡
ፍልሰት ተፈጥሯዊና ህገመንግስታዊ መብት ከመሆኑም ባሻገር ጠቀሜታው የጎላና ከሰው ልጅ የኑሮ ዑደት ጋር አብሮ የዘለቀና የሚኖር ነባራዊ እውነታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ፍልሰት ዓለም አቀፋዊ የሰብዓዊ መብት፣ የፖለቲካ፣ የጸጥታና የልማት አጀንዳ እንዲሁም ከዓለም አቀፍ የትብብር መስኮች አንዱ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ፍልሰት የመነሻ፣ መተላለፊያና መዳረሻ ሀገራት የመልማት እድል በማስፋት ለ2030 የዘላቂ ልማት ግቦች መሳካት አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግም ነው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት፡፡
ፍልሰት በአግባቡ ከተመራ የማደግና የልማት ዕድልን እንደሚፈጥር ገልጸው፥ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የፍልሰትን ጉዳይ በአስር ዓመቱ የልማት እቅድ እንዲካተት አድርጋለች ብለዋል፡፡
በለይኩን ዓለም