አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ አወጣጥ፣ የክትትልና ቁጥጥር ስራን በጥናትና ምርምር በመደገፍ እያከናወነ ነው አሉ አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ።
አምስተኛው ዓመታዊ የፓርላማ ጥናትና ምርምር ኮንፍረንስ “አካታችና ጠንካራ የፓርላማ ስርዓት ለሀገር በቀል እውቀትና ቀጣይነት ላለው ልማት በሚል መሪ ሃሳብ መካሄድ ጀምሯል፡፡
በዚሁ ወቅት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ እንዳሉት፤ የምርምር ባህልን ማሳደግ ቀጣይነት ላለው እድገት፣ ጠንካራ ምጣኔ ሃብትና ዘላቂ እድገት መረጋገጥ ወሳኝ ነው።
በመሆኑም የምርምር ኮንፍረንሱ ምክር ቤቱ ለሚያወጣቸው ፖሊሲዎች፣ ህጎችና ለሚያደርገው የክትትልና ቁጥጥር ሥራ ያላቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ምክር ቤቱ የሕግ አወጣጥ፣ የክትትልና ቁጥጥር፣ የሕዝብ ውክልና እና የፓርላማ ዲፕሎማሲ ሥራዎችን በጥናትና ምርምር የተደገፉ እንዲሆኑ በማድረግ የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ እየሰራ ነው ብለዋል።
የህዝብ ቅሬታን በጥናትና ምርምር በመለየት በሚወጡ ህጎችና ፖሊሲዎች በማካተት ዘላቂ መፍትሔ እንዲሰጣቸው እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይም ከምርምር ተቋማት ጋር ያለው ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።