Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሲዳማ ክልል 13 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ገቢ ሰበሰበ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሲዳማ ክልል ገቢዎች ቢሮ በ2017 በጀት ዓመት 13 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ገቢ ሰበሰበ፡፡

በቢሮው የደንበኞች አገልግሎት የታክስ አወሳሰንና አሳባሰብ ዘርፍ ሃላፊ ወ/ሮ ሙላት ዮሴፍ እንዳሉት÷ በበጀት ዓመቱ ከሁሉም አማራጮች የሚገኘውን ገቢ በሚገባ ለመጠቀም በትኩረት ተሰርቷል፡፡

ከመደበኛ ግብር ከፋዮችና ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት 15 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱንም አስረድተዋል፡፡

የገቢ አሰባሰብ ሒደቱን ለማሳለጥ ለባለሙዎች የአቅም ግንባታ ሥልጠና ከመስጠት ባለፈ አዳዲስ አሰራሮች መተግበራቸውን ነው ያብራሩት፡፡

በዚህም በበጀት ዓመቱ 13 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በመሰብሰብ የአቅዱን 89 በመቶ ማሳካት መቻሉን ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡

በክልሉ 45 ሺህ በላይ ግብር ከፋዮች መኖራቸውን የጠቀሱት ወ/ሮ ሙላት÷ በወቅቱና በታማኝነት እንዲከፍሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ተከናውኗል ብለዋል፡፡

ከብልሹ አሰራርና ከግብር ሥወራ ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ አካላት ላይ አስተዳደራዊ እና ሕጋዊ ርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝም አመልክተዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

Exit mobile version