Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የህዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ሕብረብሔራዊ አንድነት ከፍ እንዲል ሰርቷል – ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የህዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ኢትዮጵያዊነት እንዲደምቅ እና ሕብረብሔራዊ አንድነት ከፍ እንዲል ሰርቷል አሉ የብልፅግና ፓርቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)።

በብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽ/ቤት የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማ በአርባምንጭ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) በመድረኩ እንዳሉት፤ በብዝሃነት ውስጥ የደመቀች ኢትዮጵያ እየተጠናከረች እንድትሄድና ጽንፈኝነት እንዲከስም፣ የአንድነት፣ የአብሮነት፣ የወንድማማችነት መንገድ ብቸኛው አዋጭ የለውጥ መንገድ መሆኑን ኢትዮጵያውያን እንዲረዱ ተሰርቷል።

በኢትዮጵያ ዘመናዊ የፖለቲካ ባሕል እንዲፈጠር፣ በንግግርና ምክክር የሚያምን ከስሜት የፀዳ የፖለቲካ እሳቤ እና ተግባር እየሰረፀ እንዲሄድ የሚያስችል የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ ተከናውኗል ነው ያሉት።

በአጠቃላይ የህዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ኢትዮጵያዊነት እንዲደምቅና ሕብረብሔራዊ አንድነት ከፍ እንዲል ሰርቷል ያሉት ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)፤ በዚህ ረገድ ዘርፉ በስፋት እየሰራ ያለውን ተግባር አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።

2017 ዓ.ም ለኢትዮጵያ ልዩ ዓመት ነው ያሉት ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)፥ ኢትዮጵያዊነት እንዳይቀጥል ሕዝቧ በዘር በሐይማኖት እንዲከፋፈል ከፍተኛ ጥረት ያደረጉ፣ በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር ለማድረግ የሰሩ አካላት እየከሰሙ የመጡበት ዓመት መሆኑን አብራርተዋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያዊነት ጎልቶ በመውጣት በብዝሃነት ውስጥ የደመቀ የሕብረብሔራዊ አንድነት ትርክት እየጎለበተ መጥቶ ኢትዮጵያ ከራስ ባለፈ ለሌላው መትረፍ የጀመረችበት ዓመት ነበር ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን ለአንድነትና ሰላም የሚበጅ አጀንዳ ቀርፀው በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አማካኝነት አካታች ውይይት የጀመሩበት እና ሕዝቦች ከድህነት ለመውጣት እርዳታ ሳይጠብቁ ‘እኛው ለኛው መድኃኒት ነን’ በሚል በሁሉም የኢኮኖሚ መስኮች ለውጥ ያዩበት እንደሆነ ገልጸዋል።

በዲፕሎማሲው መስክ የባህር በር ጥያቄ ትልቅ አጀንዳ የሆበት እና ዓለምም የጥያቄውን ወሳኝነት የተገነዘበበት ዓመት እንደነበረ አንስተዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በአንድነት ሰርተን ለምረቃ ዋዜማ የደረስንበት ስለሆነ ይሄንን ብስራት ለዓለም የማሳወቅ ኃላፊነትቱን የኮሙኒኬሽንና ሕዝብ ግንኙነት ዘርፉ እንዲወጣ አስገንዝበዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ ገብረመስቀል ጫላ በበኩላቸው፥ መንግስት ለሕዝብ የገባውን ቃል እያሳካ እንደሆነ ለማሳየት የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ብለዋል።

ሕዝብ ትክክለኛ መረጃ የማግኘት መብት አለው በማለት ገልጸው፤ በዚህ በድህረ እውነት ዘመን የመረጃ አማራጮች በመስፋታቸው ትክክለኛውን ለይቶ የማስተዳደርና የማስገንዘብ ድርሻ መወጣት ይገባል ብለዋል።

በመለሰ ታደለ

Exit mobile version