አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ በዛሬው ዕለት በየካ ተራራ በመገኘት የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አከናውነዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ታዬ በዛሬው ዕለት ያከናወኑት የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ከፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ሠራተኞች እና አመራሮች ጋር በመሆን ነው፡፡
በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት እንዲያንሰራራ አድርጓል ብለዋል።
መርሐ ግብሩ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ጫናን ለመቋቋም በምታደርገው ጥረት ዓለም አቀፍ እውቅና እንድታገኝ ማድረጉን ተናግረዋል።
አረንጓዴ አሻራ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው በመግለጽ፤ ህብረተሰቡ በችግኝ ተከላ እና በመንከባከብ ረገድ ያለውን አስተዋጽኦ እንዲያጠናክር አጽንኦት ሰጥተዋል።
በመትከል ማንሰራራት በሚል መሪ ሀሳብ የዘንድሮ አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እየተካሄደ ሲሆን፤ በመላ ኢትዮጵያ ችግኝ እየተተከለ ይገኛል።