አበባ፣ ሐምሌ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል በ2017 በጀት ዓመት በኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ዘርፎች በርካታ ውጤታማ ሥራዎች ተከናውነዋል አሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ፡፡
የኦሮሚያ ክልል የ2017 በጀት ዓመት የመንግስትና የፓርቲ የሥራ አፈጻጸም ግምገማ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡
አቶ ሽመልስ አብዲሳ በመድረኩ ባደረጉት ንግግር ፥ በክልሉ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በርካታ ተስፋ ሰጪ እና አበረታች ሥራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል፡፡
በዚህም በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች የሕዝቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቁመው÷ ያጋጠሙ ፈተናዎችን ወደ እድል በመቀየር ዓመቱን በስኬት ማጠናቀቅ መቻሉን አስገንዝበዋል፡፡
በሥራ እድል ፈጠራ፣ የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀምን በማዘመን፣ገቢን በማሳደግና የአርብቶ አደሩን ሕይወት መለወጥ በሚያስችሉ ተግባራት ላይ በትኩረት መሰራቱንም ጠቅሰዋል።
መድረኩ የተጠናቀቀው በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም በጥልቀት የሚፈተሽበትና ጠንካራና ደካማ ጎኖች ተለይተው ለ2018 በጀት ዓመት አቅጣጫ የሚያዝበት መሆኑን አመላክተዋል።
አዲሱ የበጀት ዓመት ለሕዝቡ ቃል የገባንበት ሁለንተናዊ የልማት መስኮች ለማሳካት በሙሉ አቅማችን የምንረባረብበት ዓመት በመሆኑ በየደረጃው ያለው አመራር ራሱን ማዘጋጀት አለበት ሲሉም አሳስበዋል።
ለአገልግሎት አሰጣጥ እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ ብልሹ አሰራሮች፣ ሌብነት፣ ሕገ ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ፣ የጎጠኝነትና የጥቅም ጥገኝነት አመለካከቶችና አስተሳሰቦችን ለማምከን መረባረብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ከፍያለው ተፈራ በበኩላቸው ፥ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ጠንካራ የመንግስትና የፓርቲ አደረጃጀትና አሰራር ለመፍጠር አበረታች ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።
የቀበሌ አደረጃጀትና መዋቅር በመዘርጋት በተለይም ሕዝቡ በቅርበት አገልግሎቱን እንዲያገኝ መቻሉን ጠቅሰው÷ በዚህም በክልሉ የተሻለ ሰላም በማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎች ማከናወን መቻሉን አመልክተዋል፡፡