Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኮሮና ያደርሳል ተብሎ ከተተነበየው አስከፊ ጉዳት ታድጎናል – አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 7 ፣ 2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የኮሮና ቫይረስ ያደርሳል ተብሎ ከተተነበየው አስከፊ ጉዳት ታድጎናል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ።
 
የአስቸካይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጻም መርማሪ ቦርድ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ለተቋቋመው የሚኒስትሮች ኮሚቴ የመስክ ምልከታ ግብረ መልስ አቅርቧል።
 
የቦርዱ አባላት በኦሮሚያ፣ አማራና የደቡብ ብሔር፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልሎች በማቅናት የመስክ ምልከታ ማድረጉ ተገልጿል።
 
በዚህም በዝግጅት ምዕራፍ በተከናወኑ ተግባራት በተለይ ቫይረሱን ለመከላከል የሚያስችሉ አደረጃጃቶችን በአጭር ጊዜ በማቋቋም ረገድ ጠንካራ ስራ መሰራቱን አባላቱ ተናግረዋል።
 
የምርመራ አቅምን በማሳደግ ረገድ የተከናወነው ስራንም በመልካም ጎኑ አንስተዋል።
 
በአዋጁ አፈጻጸም ወቅትም ምንም አይነት የሰብዓዊ መብት ጥሰት አለመከሰቱን ተናግረዋል።
 
በድንበሮች አካባቢ በቂ የቁጥጥር ስርዓት አለመኖሩንና በማህበረሰቡ ዘንድ መዘናጋቶች መኖራቸውን ደግሞ በድክመት ለይተዋል።
 
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አዋጁ ቫይረሱ ሊያስከትል ከሚችለው ከፍተኛ ጉዳት ታድጎናል ነው ያሉት።
 
በማህበረሰብ አቀፍ የመከላከል፣ ምርመራና ንቅናቄ አማካኝነትም እስከታችኛው የህብረተሰብ ክፍል ድረስ በመውረድ ቫይረሱን የመከላከል ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
 
በድንበሮች አካባቢ ያለውን የሰዎች እንቅስቃሴ ለመገደብም ከክልሎች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
 
ኢትዮጵያን በቫይረሱ የከፋ ጉዳት ሳይደርስባት ወደ መጪው ዘመን ለማሸጋጋርም ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
 
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።
Exit mobile version