Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተለያዩ ርምጃዎች እየወሰደች ነው – ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ከቤተሰብ ጀምሮ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተለያዩ ርምጃዎች እየወሰደች ነው አሉ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ።

በአዲስ አበባ እየተካሄደ ካለው የተባበሩት መንግስታት የምግብ ሥርዓት ጉባኤ ጎን ለጎን እየተካሄደ በሚገኘው የ2025 የዓለም የምግብ ዋስትናና የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ሁኔታን የተመለከተ ሪፖርት ይፋ ማድረጊያ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል።

በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በዓለም ላይ እየጨመረ የመጣው የምግብ ዋጋ የጋራ መፍትሔ ያስፈልገዋል ብለዋል።

የምግብ ዋጋ መናር በተለይም አነስተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎችን የበለጠ የሚጎዳ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህን ችግር ለመፍታት ሀገራት የጋራ ትብብርና መፍትሔ ሊኖራቸው ይገባል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናዋን ለማረጋገጥ የተለያዩ ርምጃዎችን እየወሰደች ጠቅሰው፤ በተለይም በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ውጤታማ መሆኑን ገልጸዋል።

በሴፍትኔት መርሐ ግብርም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ አንስተዋል።

በዓለም ላይ አስተማማኝ የምግብ አቅርቦትን ለማረጋገጥ ሰላምን ለማፅናት ሀገራት በጋራ ሊቆሙ እንደሚገባም ነው ያመለከቱት።

የተባበሩት መንግስታት ምክትል ዋና ጸሐፊ አሚና መሀመድ በበኩላቸው፤ በምግብ ዋጋ እየጨመረ መምጣት በርካታ የዓለም ዜጎች የምግብ ዋስትናቸው እንዳይረጋገጥ አድርጓል ብለዋል።

የአየር ንብረት ለውጥና የተለያዩ ግጭቶች የዓለም የምግብ አቅርቦትና ዋጋ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደራቸውንም ገልጸዋል።

በርካታ ህፃናት በምግብ እጥረት ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው መቅረታቸውንም ነው ያነሱት።

በዓለም ላይ ግጭትን ማስቀረት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለዚህ ደግሞ የጋራ ትብብርና ተግባራዊ እርምጃ ያስፈልጋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

Exit mobile version