Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለኢኮኖሚ እድገት አስተዋፅኦ እያደረገ ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገ ይገኛል አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በሶማሌ ክልል ጂግጂጋ ከተማ ተገኝተው አሻራቸውን አኑረዋል።

በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ባለፉት 7 ዓመታት ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አስተዋፅኦ የሚያደርጉ የተለያዩ ዓይነት ችግኞች ተተክለዋል ብለዋል።

ለኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያደርጉ እንደ ቡና እና አቮካዶ አይነት ተክሎች በመርሃ ግብሩ በስፋት መተከላቸውን ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከፍተኛ እድገት አሳይቷል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ አረንጓዴ አሻራ ለኢኮኖሚ እድገቱ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጉን ጠቅሰዋል፡፡

በተለይም ዝናብ አጠር አካባቢዎች የሚተከሉ ችግኞች ተፈጥሯዊ ስነ ምህዳር ለማስተካከል ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል ብለዋል፡፡

አርብቶ አደር የነበረው የሶማሌ ክልል ከለውጡ በኋላ ከፍተኛ የግብርና ምርት እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብሩ የክልሉን የአምራችነት አቅም የበለጠ ያጠናክረዋል ነው ያሉት፡፡

በአንድ ጀንበር 700 ሚሊየን ችግኞች የመትከል መርሐ ግብር በመላው ኢትዮጵያ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው÷ ህብረተሰቡ በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በሚኪያስ አየለ

Exit mobile version