አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) የ2017 በጀት ዓመት ባለተሰጥኦ አዳጊዎች የሳይበር ስልጠና መርሐ ግብር በይፋ ተጀመረ።
ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የተውጣጡ 700 የባለ ልዩ ተሰጥዎ ባለቤት አዳጊዎች የሚሳተፉበትን ይህን መርሐ ግብር ኢመደአ እና አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በጋራ በመሆን ነው ያዘጋጁት።
በመርሐ ግብሩ መክፈቻ ላይ የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚድ እንዳሉት፤ መርሐ ግብሩ የባለ ልዩ ተሰጥኦ አዳጊ ወጣቶችን ሕልም ከተጨባጭ ዕድል ጋር ያገናኛል።
በተጨማሪም የዲጂታል ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ሂደት ውስጥ የማይተካ ሚና የሚጫወት የሰው ኃይል የማፍራት እንቅስቃሴ አካል መሆኑን ተናግረዋል።
ሰልጣኝ አዳጊዎቹ በቆይታቸዉ በዕውቀት፣ በአስተሳሰብ እና በሥነ ምግባር በመታነጽ ሀገራዊ የዲጂታላይዜሽን ጉዞን መደገፍ እንዳለባቸዉ አስገንዝበዋል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት በአዲስ አበባ ብቻ ተወስኖ የነበረውን መርሐ ግብር ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በባሕር ዳር ከተማ 84 ባለልዩ ተሰጥኦ አዳጊዎችን በመያዝ በቅርቡ ወደ ተግባር እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ከድር ኢብራሂም (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ተቋማቸው ከኢመደአ ጋር በመተባበር የተለያዩ ጉዳዮች ላይ እየሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።
በተለይ በሳይበር ታለንት ልማት ዘርፍ ምሳሌ የሚሆን ስራ በጋራ ተሰርቷል ማለታቸውን የኢመደአ የኮሙኒኬሽን እና ሳይበር ባህል ግንባታ ማዕከል ዳይሬክተር ቴዎድሮስ ኃይሉ ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል።
በሶስና አለማየሁ