Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰኔ እና ሐምሌ 2017 ዓ.ም ቁልፍ ተግባራትን አከናውነዋል

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሰኔ እና በሐምሌ ወር 2017 ዓ.ም ቁልፍ የሆኑ ብሔራዊ የፖሊሲ ትግበራን፣ የኢኮኖሚ ሪፎርምን፣ ቀጠናዊ እና ዓለማቀፋዊ ስትራቴጂካዊ ዲፕሎማሲን በሚያሳልጥ መልኩ ተከታታይ ተግባራት አከናውነዋል።

በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሀገር ውስጥ ካከናወኗቸው ተግባራ መካከል፤ የ2017 የዕቅድ አፈጻጸምን አስመልክቶ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ሰፊ ምላሽና ማብራሪያ የሰጡበት ይጠቀሳል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ17ኛው BRICS የመሪዎች ጉባኤ ላይ በመሳተፍ፣ ከዓለም መሪዎች ጋር ባደረጉት የላቀ ስትራቴጂካዊ አጋርነት የኢትዮጵያ ስም ከፍ እንዲል አድርገዋል።

ሌላው የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ የታየበት ሁነት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሁለተኛው የምግብ ስርዓት ጉባኤ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ በጋራ ያዘጋጀችው ትልቅ አለማቀፍ ጉባኤ ነበር።

እነዚህ የከፍተኛ ደረጃ ተሳትፎዎች(High-level engagements) ሀገራዊ ልማትን ለማፋጠን እና ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ያላትን ሚና በከፍተኛ ሁኔታ ለማጎልበት ያለመ አመራር እንደተሰጠ ያረጋግጣል።

በሰኔ ወር መጨረሻ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የመንግስትን የ2017 የዕቅድ አፈጻጸምን አስመልክቶ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ሰፊ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ማበራሪያቸው ኢትዮጵያ እያከናወነች ባለቸው ጥልቅ የኢኮኖሚ ሪፎርም እና የምጣኔ ሀብታዊ ማሻሻያዎች፤ እንዲሁም በሂደቱ እየተመዘገቡ ስለሚገኙ ስኬቶች እና ተግዳሮቶች በሰፊው አስረድትዋል።

ለአብነትም የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያን በተመለከተ ማበራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ወደ ማክሮ ኢኮኖሚ ያስገቡን ጉዳዮች አንዱ የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራቶች ናቸው፤ በስራ አጥነት፣ በዋጋ ግሽበት፣ በወጪና ገቢ ንግድ ሚዛን መጓደል ሊገለፅ የሚችል ነው ብለዋል።

ሁለተኛው ለግሉ ዘርፍ የስራ አካባቢው ምቹ አልነበረም። ሶስተኛው ምርታማነት ነው። በግብርናም በኢንዱስትሪም ምርታማነታችን ውስን ነበር። ይህም በርካታ ተግዳሮቶች እነዲስተናገዱ አድርጓል።

አራተኛው ተወዳዳሪ የኢኮኖሚ ሁኔታን አልፈጠርንም ብለዋል። እነዚህን ጉዳዮች ጨክነን በመፍታት የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራቱን መፍታት እንችላለን ብለን ነው ወደ ተግባር የገባነው ሲሉ ነው ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጠቆሙት።

እንደ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ መንግስት ባደረገው ውጤታማ የሪፎርም ስራዎች እና በተደረገው ሁሉን አቀፍ ርብርብ፤ በ2017 በጀት ዓመት በወሳኝ የልማት ዘርፎች ማለትም በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በአገልግሎት፣ በፋይናንስ፣ በውጭ ንግድ እና ሌሎችም አበረታች ስኬቶች ስለመመዝገባቸው ለምክር ቤት አባላቱ አብራርተዋል።

በዚሁ ማብራሪያቸው ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሰላምና ጸጥታን በተመለከተ ግልጽ ማብራሪያ ያቀረቡ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሰላምና የጸጥታ ችግር ዋነኛው መንስኤ የተሳሳተ የፖለቲካ አመለካከት እንደሆነ አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ በጎረቤት ሀገራት ዘንድ የምትከተለውን የዲፕሎማሲ አና አሁናዊ እንቅስቃሴ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሲያብራሩ ደግሞ፤ ሀገሪቱ ከጎረቤቶቿ ውጭ ህልውና የላትም ብለዋል።

በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ባለፉት ሰባት ዓመታት ከየትኛውም የጎረቤት ጋር ግጭት ውስጥ እንዳልገባች በመግለጽ፤ ሀገራቸው በቀጣናው ሰላማዊ ግንኙነት ያላትን ቁርጠኝነት አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በ17ኛው የብሪክስ ጉባኤ ለመሳተፍ ወደ ሪዮዲጀኔሮ ባቀኑበት ወቅት፣ ከጉባኤው አስቀድሞ ከብራዚል ፕሬዝደንት ሉዊዝ ኢናቺዮ ሉላ ደ ሲልቫ ጋር ተገናኝተን በሁለትዮሽ እና በባለብዙ ወገን ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል።

የሁለቱ መሪዎች ውይይትም በቅርብ እያደገ የመጣውን የሀገራት ግንኙነት የበለጠ በማጠናከር ረገድ አንድ ርምጃ ወደፊት የወሰደ ነበር።

በተለያዩ ዘርፎች የንግድ እና ኢንቨስትመንት ትስስሮቻቸውን የበለጠ ለማጠናከር መሪዎቹ ተስማምተዋል። በተመሳሳይ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኪያንግ ጋር 55 ዓመታትን ባስቆጠረው የኢትዮ-ቻይና ግንኙነት ላይ ውይይት አድርገዋል።

ግንኙነታቸው በሁኔታዎች ሁሉ እንደማይቀያየር አጋሮች (all weather strategic partners) ባለፉት ሰባት ዓመታት ትብብራችን ጉልህ ፍሬዎችን አፍርቷል።

ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን እና አይሲቲን ባካተቱ ቁልፍ የኢኮኖሚ ዓምዶች ላይ የሀገራቱ ትኩረት እንዳለ ሆኖ ሌሎች የትብብር መስኮችን ለማጠናከርና እንደ አርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ፣ ሎጂስቲክስ እና ንጹሕ የኃይል ምንጮች ልማት ላይ ያላቸወን ዕምቅ ዐቅም ለመመልከትም መሪዎቹ ችለዋል።

በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሪዮ ዲ ጄኒሮ በተካሄደው 17ኛው የብሪክስ ጉባኤ የሰላም፣ የፀጥታ እና አለምአቀፍ አመራር መድረክ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ስኬታማ ትብብርን ለማስቻል አፀፋዊ መተማመንን የሚያሳድጉ ዓለምአቀፍ ተቋማት የመኖርን አጣዳፊነት አንስተዋል።

ዓለምአቀፍ የገንዘብ ተቋማት የጋራ ደኅንነትን እና ሁሉን አካታች ብልጽግናን ለማምጣት ይረዳ ዘንድ የውሳኔ አሰጣጥ መዋቅራቸው ምሉዕነት ባለው መልክ የሚሻሻልበትን ሁኔታም አፅንኦት ሰጥተው አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በይፋ ወደ ብሪክስ የተቀላቀለችው በ2015 ዓ.ም ሲሆን ኢኮኖሚያዊ ወዳጅነት ብቻ ሳይሆን ፍትኃዊ የሆነ፣ እኩልነት የሚሰፍንበት ብዝኃ ዋልታዊ አለምን ለመፍጠር ከሚተጉ ሀገራት ጋር በእኩል ደረጃ የተሰለፈችበት ስብስብ ነው።

እንደ ብሪክስ አባልነቷ ኢትዮጵያ እነዚህ ጥረቶች እንዲሳኩ በተለይም በአለምአቀፍ ውሳኔ ሰጪ መድረኮች ለአዳዲስ ገበያዎች እና በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት ሰፋ ያለ ውክልና በሚገኝበት ሁኔታ ላይ በንቃት አስተዋፅኦ ታደርጋለች። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የብሪክስን እያደገ የመጣ ተፅዕኖ ሲገልጹም የሚከተለውን ብለዋል።
”ብሪክስ ከጠንካራ አዲስ ሀሳብ ተነስቶ ለአለምአቀፍ ለውጥ የሚሰራ ብርቱ ኃይል ወደመሆን ተሸጋግሯል። አዳዲስ አባላት በመጨመራቸውም የጋራ ድምፃችን የበለጠ ይጠናከራል። የጋራ አላማችን የበለጠ ይጠራል። አቅማችንም ይሰፋል።” ኢትዮጵያ በ2017 የሥራ ዘመን ትርጉም ያለው እና ለመጪው የ2018 የቀጠለ የእድገት ጉዞ ጠንካራ መሠረት የሚሆን እድገት ፈጽማለች።

በዚህ መነሻነትም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላትን በመሰብሰብ ለመጪው ዓመት ለትግበራ የተዘጋጀውን የ2018 የተሟላ የሁሉም ዘርፎች እቅድ እና ሀገራዊውን የልማት እቅድን ገምግመዋል።

እንዲሁም በሐምሌ ወር ኢትዮጵያ ለሶስት ቀናት በአዲስ አበባ በስኬት የተከናወነውን ሁለተኛውን የተባበሩት መንግሥታት የምግብ ሥርዓት ጉባኤ በጋራ ማዘጋጀቷን ተከትሎ፣ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተለተለያዩ ሀገራት መሪዎችን እና የዓለም አቀፍ ተቋማት ሀላፊዎችን ተቀብለው አነጋግረዋል።

በዚህም (የጣሊያኗን ሪፐብሊክ) ጠቅላይ ሚኒስትር ጂኦርጂያ ሜሎኒን ጨምሮ (የኬንያውን ሪፐብሊክ) ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶን፣ (የሶማሊያውን) ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼህ መሃሙድ እና (የኮሞሮስ ህብረት) ፕሬዝዳንትን አዛሊ አሱማኒ በመቀበል በሁለትዮሽ፣ ቀጣናዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

በተጨማሪም ከዚሁ ጉባኤ ቀደም ብሎ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተባበሩት መንግሥታት ምክትል ዋና ፀሐፊ የሆኑትን አሚና መሃመድን እና ሌሎች የዓለም አቀፍ ተቋማት ሃላፊዎችን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

በዚሁ ውይይት በመላው አፍሪካ እና በተቀረውም አለም ዘላቂ፣ አካታች እና በተለያዩ ፈተናዎች የማይበገር የምግብ ሥርዓት አስፈላጊነትን ጨምሮ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍሬያማ ውይይት አድርገዋል።

በውይይቱ ኢትዮጵያ በተቀናጁ ፖሊሲዎቿ፣ ለአየር ንብረት ጥበቃ ምላሽ ሰጪ በሆነ የግብርና ሥራዋ ብሎም በምግብ ዋስትና እና ለሁሉም የተመጣጠነ ምግብ በማቅረብ ማኅበረሰብ መር ዘዴዎቿ የምግብ ሥርዓትን ለማሻሻል ባላት ፅኑ አቋም እና ተግባር መቀጠሏን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስምረውበታል።

በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሁለተኛው የተባበሩት መንግሥታት የምግብ ሥርዓት ጉባኤ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል።

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው እንደገለጹት በገጠር መሠረተ ልማት እና በሥነ-ምግብ ላይ የሚደረጉ ኢንቨስትመንቶችን ለማጎልበት ተገማች የሆነ የኮንሴሽናል ፋይናንሺንግ አስፈላጊነትን አጽንኦት ሰጥተዋል።

በዚሁ የመክፈቻ ንግግራቸው ኢትዮጵያ በምግብ ስርዓት ሽግግር ያደረገችውን ስኬታማ ጉዞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያብራሩ ሲሆን፤ በሀገር ውስጥ የምርት እድገት ላይ ኢንቨስትመንትን በማሳደግ፣ ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ያለውን ጥገኝነት በመቀነስ እና ለትውልዱ በቀጣይ ፈተናዎች የማይበገር ስርዓትን እውን በማደረግ ሂደት አመርቂ ውጤት መገኘቱን ጠቁመዋል።

በወቅቱም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተባበሩት መንግስታት የምግብ ስርዓቶች ጉባዔን አስመልክቶ ለክብር እንግዶች በብሔራዊ ቤተ መንግሥት እራት ግብዣ አሰናደተዋለ።

በጥቅሉ በሰኔ እና ሐምሌ ወር 2017 ዓ.ም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከፍተኛ የሆነ ሀገራዊ የፖሊሲ ግምገማዎች እንዲደረጉ፣ ጉልህ የሆኑ አለም አቀፍ ስብሰባዎች እንዲከናወኑ እና በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ተሳትፎ እንዲፈጠር በሳል አመራር የሰጠበት ነው።

ሁሉም ተግባራት የኢትዮጵያን ዕድገት እውን ለማድረግ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለትን ስትራቴጂካዊ አስፈላጊነት ለማጉላት የታለሙ ስኬታማ ክንውኖች ነበሩ።

Exit mobile version