Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮጵያ ማንሰራራት ከትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ጋር የተሳሰረ ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ማንሰራራት ከትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ዘርፍ ማንሰራራት ጋር የተሳሰረ ነው አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮ-ጂቡቲ የምድር ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበር የሰራተኞች ቀን በዓል ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፥ የኢትዮ-ጂቡቲ የምድር ባቡር የኢትዮጵያውያን የአሸናፊነት ውጤት ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮ-ጂቡቲ የምድር ባቡር የኢትዮጵያ ወጪና ገቢ ንግድ ዋና መተላለፊያ መስመር መሆኑን ጠቅሰው፥ መስመሩን ተከትለው በርካታ ከተሞች መቆርቆራቸውንና በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ወሳኝ ሚናን የተጫወተ የሚገኝ መሠረተ ልማት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የተቋሙን አገልግሎት አሰጣጥ የመቀየር ሪፎርም ባለፉት ሰባት የለውጥ ዓመታት መንግሥት ከወሰዳቸው በርካታ የሪፎርም ሥራዎች መካከል አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በተለይም ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ ኢትዮጵያ እና ጂቡቲ የባቡር መሥመሩን ከቻይናዊያን አስተዳደር በመረከብ የላቀ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ ሲሠራ ቆይቷል ነው ያሉት፡፡

መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ልዩ ትኩረት በሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ የተደገፉ አሠራሮች መዘርጋታቸውን ተከትሎ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን መመልከት ችለናል ብለዋል፡፡

የባቡር መስመሮች የሀገሪቱን ዕድገት ባገናዘበ ደረጃ ኢትዮጵያን በውስጥም በውጭም እስኪያገናኙ ድረስ የዘርፉ ሪፎርም ቀጣይነት እንዲኖረው በትጋት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ኢትዮጵያን የዘመናዊ ባቡሮች ሀገር ማድረግ አለብን ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በዘርፉ ራሳችንን እያስተማርንና እያበቃን፣ በትብብርና መደጋገፍ መንፈስ ታሪክ ለመስራት መትጋት ይጠበቅብናል ብለዋል።

መንግሥት በትናንት ውጤቶች ሳይረካና በዛሬ ሳይታጠር ነገን ዛሬ ላይ በመሥራት ይተጋል ሲሉ ነው የገለጹት፡፡

የኢትዮ-ጂቡቲ የምድር ባቡር ትራንስፖርት 130 ዓመታትን ያስቆጠረ አንጋፋ ተቋም ነው።

በለይኩን ዓለም

Exit mobile version