አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተለያዩ የግብርና ምርምር ሥራዎችን በማከናወን ዘርፉን ለማሳደግ እየሰራ ነው አሉ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አስራት አጸደወይን (ዶ/ር) ።
አስራት አጸደወይን (ዶ/ር) ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአርሶ አደሮችን ቀን ባከበረበት ወቅት እንዳሉት÷ ተቋሙ በግብርናው ዘርፍ ላደረጋቸው የምርምር ሥራዎች አርሶ አደሮች ከፍተኛ እገዛ አድርገዋል።
አርሶ አደሮች በዩኒቨርሲቲው ምስረታና ሒደት ከፍተኛ አበርክቶ እንደነበራቸው ጠቁመው ÷ ተቋሙ የአርሶ አደሮችን ውለታ መቼም አይዘነጋም ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው በግብርናው ዘርፍ ላይ የጀመራቸውን ጥረቶች በቀጣይ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አወቀ አስፈሬ በበኩላቸው÷በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት ተቋማት በቴክኖሎጂ ማገዝ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ በግብርናው ዘርፍ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ባከናወናቸው ሥራዎች የላቀ አበርክቶ ለነበራቸው አርሶ አደሮችና ተቋማት እውቅና ተሰጥቷል፡፡
በምናለ አየነው