አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ የኮሪደር ልማት የኢትዮጵያ ብልጽግና አይቀሬ መሆኑን ከምናረጋግጥባቸው ስራዎች መካከል አንዱ ነው አሉ፡፡
የብልፅግና ፓርቲ ምክር ቤት አባላት ከእንጦጦ እስከ 4 ኪሎ ፕላዛ ድረስ የተሰራውን የ5 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል፡፡
አቶ አደም ፋራህ በጉብኝቱ ወቅት እንዳሉት÷ የኮሪደር ልማት ከኢትዮጵያ ባለፈ ለሌሎች ታዳጊ ሀገራት የከተማ ልማት አመራር ደረጃ መለኪያ እየሆነ ያለ ስራ ነው።
የኮሪደር ልማቱ የፓርቲያችን መፍጠን እና መፍጠር መርህ በተግባር እየተረጋገጠበት ያለ ስራ ነው በማለት ገልጸው፤ ስራው ለኢትዮጵያ በሚመጥን መልኩ በትልቁ ታስቦ በጥራት፣ በጊዜ፣ ህዝቡን በላቀ ደረጃ ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ መጨረስ የሚለው እሳቤ በትክክል የታየበት መሆኑን ተናግረዋል።
የኮሪደር ልማት ከተሞች ለሀገር ኢኮኖሚ ማበርከት ያለባቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረከቱ ከማስቻል አንጻር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ገልጸው፤ ስራው የአመራራችን ቁርጠኝነት በተግባር የታየበት ነው ብለዋል።
ባለሙያዎች በትብብር ከሰሩ እና ህዝቡ በሀገራዊ ልማት ስራዎች ላይ መሳተፍ ከቻለ በአጭር ጊዜ ውጤታማ ስራ መስራት እንደሚቻል መታየቱንም ገልፀዋል፡፡
የኮሪደር ልማት ስራው ከተሞች ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲገነቡ አድርጓል ያሉት አቶ አደም ፋራህ÷ ይህም ቀደም ሲል ከተሞችን የምናይበትን መነፀር ሙሉ በሙሉ ቀይሯል ነው ያሉት።
በሚኪያስ አየለ