Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ጤናማ የወንዝ ዳርቻዎች የማህበረሰብን የኑሮ ደህንነት ለማሻሻል ያስችላሉ – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጤናማ የወንዝ ዳርቻዎች የማኅበረሰብን የኑሮ ደህንነት የሚያሻሽሉና የከተሞችን ለፈተና አለመበገር የሚያጠናክሩ ደማቅ ሕዝባዊ ሥፍራዎችን ይፈጥራሉ አሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ÷ ዛሬ ከሰዓት ከብልጽግና ምክር ቤት ስብሰባ በኋላ የአዲስ አበባ ሒደትን በጋራ ተመልክተናል ብለዋል።

የወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራው አሁን በተያዘው ምዕራፍ በአምስት ክፍለ ከተሞች የሚዘልቅና 21 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርዝመት እንዳለው አስረድተዋል።

በፕሮጀክቱ የእግረኛ መንገዶች፣ የብስክሌት መንገድ፣ ሕዝባዊ ፕላዛዎች፣ የመኪና ማቆሚያዎች፣ የሕፃናት መጫወቻዎች፣ ሱቆች እና አምፊቴአትሮች እንደተካተቱ አመልክተዋል።

ሥራው የወንዞችን ብክለት ማስወገድ፣ የከተማዋን የጎርፍ ተጋላጭነት መቀነስ፣ ሕዝባዊ መሠረተ ልማቶችን ማስፋፋት፣ የአረንጓዴ ስፍራዎችን ቁጥር መጨመርና የሥራ እድል መፍጠር እንደሚያስችል ጠቅሰዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ አካባቢያችንን ከመጠበቅ ባሻገር ለአዲስ አበባ ደማቅ እና ዘላቂ የወንዝ ዳርቻዎችን በማስገኘት የከተማዋን ኢኮኖሚ እና የኑሮ ደረጃ ከፍ ያደርጋል ነው ያሉት።

ጤናማ፣ በሚገባ የተጠበቁ የወንዝ ዳርቻዎች የከባቢ ሥርዓትንና የውሃ ጥራትን መጠበቅ ብቻ ሳይሆን የማኅበረሰብን የኑሮ ደህንነት የሚያሻሽሉና የከተሞችን ለፈተና አለመበገር የሚያጠናክሩ ደማቅ ሕዝባዊ ሥፍራዎችን ይፈጥራሉ ሲሉም አስገንዝበዋል።

Exit mobile version