Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ከአዲስ አበባ ውጪ ባሉ ብዙ ከተሞች ያየናቸው መሻሻሎች የተለያዩ አማራጮች እንዳሉን የሚያሳዩ ናቸው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከአዲስ አበባ ውጪ ባሉ ብዙ ከተሞች ያየናቸው መሻሻሎች የተለያዩ አማራጮች እንዳሉን የሚያሳዩ ያልተጠቀምንባቸውን አቅሞቻችንንም የሚገልጡ ናቸው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መረጃ፥ አርባምንጭ በተፈጥሮ ስሪቷ ውብ ናት፤ በከተማዋ እየተካሄዱ ያሉ የልማት ሥራዎች በቅርቡ በጎበኘንበት ወቅት የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክትን ተመልክተናል ብለዋል።

ይኽ ሥራ በመጠነ ርዕዩ ግዙፍ በመሆኑ አርባምንጭ ታላላቅ ጉባኤዎችን እንድታስተናገድ ያስችላታልም ነው ያሉት።

ከዚህ ቀደም ከነበረን ምልከታ ሰፋ ብሎ የተከናወነው የኩልፎ ወንዝ ዳርቻ ልማት ለከተማዋ ልዩ መልኮች ተጨማሪ ገጽታ ፈጥሯል ሲሉም ገልጸዋል።

ወደ አርባምንጭ ጫካ አዳዲስ የመግቢያ መንገዶች የተሠሩ መሆናቸውን ገልጸው፥ ለተራሮቹ፣ ለውሃው እና ለከባቢው ደኖች መዳረሻ በር እንደሆኑም አመልክተዋል።

እነዚህና ሌሎች ከአዲስ አበባ ውጪ ባሉ ብዙ ከተሞች ያየናቸው መሻሻሎች የተለያዩ አማራጮች እንዳሉን የሚያሳዩ ያልተጠቀምንባቸውን አቅሞቻችንንም የሚገልጡ ናቸው ሲሉም ጠቁመዋል።

ይኽ እድገት በጋራ ጥረቶቻችን ታላላቅ ነገሮችን እንደምናሳካ የሚያመለክት ግልጽ ምልክት ነው ሲሉም ነው የገለጹት።

Exit mobile version