አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በየዓመቱ ነሐሴ 13 ቀን የሚከበረው የደብረ ታቦር (ቡሄ) በዓል ሐይማኖታዊ እና ባህላዊ ይዘት አለው፡፡
ቡሄ የክረምት ጭጋግ ተወግዶ ወደ ጸሃይ ብርሃንነትና ብሩህነት በሚሸጋገርበት ወቅት ይከበራል፤ ”ቡሄ ካለፈ የለም ክረምት” ፤ “ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት” ፤ መባሉም ለዚሁ ነው፡፡
የደብረ ታቦር (ቡሄ) በዓል በሐይማኖታዊ አስተምህሮው ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ታቦር ተራራ ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበት መሆኑን የሃይማኖት አባቶች ያስረዳሉ፡፡
መጋቤ ብሉይ አዕምሮ ዘውዴ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርቲያን በመንበረ ፓትርያርክ የጠቅላይ ቤተክህነት የስብከተ ወንጌልና ሐዋሪያዊ ተልዕኮ መምሪያ የስምሪት ሃላፊ ናቸው፡፡
እንደ መጋቤ ብሉይ አዕምሮ ገለጻ÷ የደብረ ታቦር በዓል በመጽሐፍ ቅዱስ ከሚከበሩ በዓላት መካከል አንዱ ነው ፤ በዓሉ ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ይዞ ወደ ደብረ ታቦት ተራራ የወጣበትና በዚያም ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበት ነው፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ ያዕቆብ፣ ዮሃንስንና ጴጥሮስን በስጋ ከሚኖሩበት ዓለም፣ ሙሴን ከመቃብር በማስነሳት እንዲሁም ኤልያስን ከተሰወረበት ዓለም በማምጣት አንድ ላይ በደብረ ታቦር አነጋግሯቸዋል፡፡ ብርሃነ መለኮቱንም ገልጦላቸዋል ይላሉ ፡፡
ደብረ ታቦር በእየሩሳሌም የሚገኝ 572 ሜትር ከፍታ ያለው ታላቅ ተራራ ሲሆን÷ ሶስት ነገሮችን ይወክላል፤ ወንጌልን፣ ቤተክርስቲያንንና መንግስተ ሰማያትን፡፡
በዓሉ ሕያውያንና ሙታን የሚያከብሩት፤ እግዚአብሔርም የሕያውያን እና የሙታን አምላክ መሆኑን ያስረዳበት እንዲሁም ትናንት፣ ዛሬ እና ነገን ያሳየበት መሆኑን መጋቤ ብሉይ አእምሮ አስገንዝበዋል፡፡
ደብረ ታቦር በቤተክርስቲያን በረጅም ማህሌት፣ በቅዳሴ፣ በትምህርትና በሌሎች መንፈሳዊ ክንውኖች እንደሚከበር ጠቁመው÷ ከመንፈሳዊነቱ በተጨማሪ በዓሉ የአንድነት፣ አብሮነትና የመተሳሰብ ምሳሌ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዛሙርቱን ከተለያየ ቦታ ማለትም በስጋ ከሚኖሩበት ዓለም፣ ከመቃብርና ከተሰወሩበት ዓለም በማሰባሰብ በደብረ ታቦር ተራራ አንድ ሆነውና ተስማምተው በዓሉን እንዳከበሩ አስታውሰው ÷ይህም የተለያየ የኑሮ ደረጃ፣ የተለያየ ባህልና ቋንቋ ያላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች መረዳዳትና መቻቻል እንዳለባቸው ያስተምራል ነው ያሉት፡፡
በሌላ በኩል ሙልሙል ዳቦ መስጠት፣ ችቦ ማብራት እና ጅራፍ ማጮህ ከደብረ ታቦር (ቡሄ) በዓል ጋር ተያይዞ የሚከናወኑ ትውፊታዊ መገለጫዎች እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡
ሙል ሙል ዳቦ ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን በገለጠ ጊዜ ብርሃን ስለሆነ የአካባቢው እረኞች/ልጆች የመሸ ስላልመሰላቸው ወደ ቤት ሳይመለሱ ቀሩ፤ በዚህ የተጨነቁ ወላጆችም ስንቅ ይዘውላቸው መሄዳቸውን ለማመላከት መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ችቦ የሚበራው ደግሞ በደብረ ታቦር ተራራ ብርሃን መገለጡን በማስመልከት ሲሆን÷ ጅራፍ የሚጮኸውም በተራራው ድምጸ መለኮት መሰማቱን ለማስታወስ ነው ይላሉ፡፡
የደብረ ታቦር (ቡሄ) በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በዛሬው ዕለት በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ይከበራል፡፡
መልካም የቡሄ በዓል!
በመላኩ ገድፍ