Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶቻችን የኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን ማሳያ ናቸው – የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ እሴቶቻችን የኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን ማሳያ ናቸው አለ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፡፡

አገልግሎቱ ለሻደይ፣ አሸንዳ፣ አሸንድዬ እና ሶለል በዓላት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል።

በመልዕክቱም ብዝኃነት እና ኅብረ ብሔራዊ አንድነት መገለጫዋ የኾነችው ኢትዮጵያ የክረምቱን መገባደድ የሚያበስሩ ትውፊቶች ባለቤት ናት ብሏል።

ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ እሴቶቻችን የኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን ማሳያ እንደሆነም አጽንኦት ሰጥቷል፡፡

አገልግሎቱ ያስተላለፈው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦

ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶቻችን የኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን ማሳያ ናቸው፡፡

ብዝኃነት እና ኅብረ ብሔራዊ አንድነት መገለጫዋ የኾነችው ኢትዮጵያ የክረምቱን መገባደድ የሚያበስሩ ትውፊቶች ባለቤት ናት።

ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ ልጃገረዶች ወደ ዐደባባይ በመውጣት የሚያሰሟቸዉ ኅብረ ዝማሬዎች በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የክረምቱን መገባደድ፤ በየጋራ ሸንተረሩ የአበቦችን መፍካት፣ የምንጮችን መጥራት እና የቡቃያዎችን ማፍራት ያበስራሉ።

ከእነዚህ ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ ክዋኔዎች መካከል ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ ለቀናት በድምቀት የሚከበረው እና በተለያዩ አካባቢዎች በተቀራራቢ ሻደይ፣ አሸንዳ፣ አሸንድዬ እና ሶለል በሚሉ መጠሪያዎች የሚታወቀው በዓል ተጠቃሽ ነው። በዓሉ በተለያዩ አካባቢዎች በተለያዩ ትውፊታዊ ዳራዎች በተቀራራቢ ዓውድ፣ በተመሳሳይ ጊዜ፣ በተለያዩ ባህላዊ ኅብረ ዝማሬዎች በሴቶች የሚከበር የነፃነት የዐደባባይ በዓል ነው። ይህን በዓል የአጎራባች ሕዝቦች ግንኙነትና ትስስርን በሚያጎለብት መልኩ ማክበር፣ መጠበቅ እና ለትውልድ ማስተላለፍ ያስፈልጋል።

ይህ በዓል ከትውልድ ትውልድ እየተወራረሰ ቢመጣም በአግባቡ ተዋውቆ አንድ የመስሕብ ሀብት እንዲኾን ተጨማሪ ሥራ ይፈልጋል። ከዚህም ባሻገር ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የሚከበሩ የተለያዩ በዓላት ጋር በማስተሳሰር ኅብረ ብሔራዊነትን በሚገነባ መልኩ መሥራት ይጠይቃል።

የጳጕሜን ቀናት፣ የኢትዮጵያ ዐዲስ ዓመት፣ የተለያዩ ብሔሮች እና ብሔረሰቦች የዘመን መለወጫ በዓላት፣ የመስቀል በዓል እንዲሁም የኢሬቻ በዓልን በቅርብ ርቀት የሚያስከትሉ በመኾናቸው የበለጠ ለጎብኝዎች ቆይታ መራዘም ጉልህ ሚና ሊጫወቱ የሚችሉ ናቸው። በመኾኑም በተለመደ ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ እሴታቸዉ መሠረት በድምቀት እየተከበሩ ለቱሪዝም ዘርፉ መነቃቃት የበኩላቸዉን ሚና እንዲጫወቱ መንግሥት አስፈላጊዉን ኹሉ ድጋፍ ያደርጋል።

እንኳን ለሻደይ/አሸንዳ/አሸንድዬ/ሶለል በዓል አደረሳችሁ!

የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

ነሐሴ 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Exit mobile version