አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሁሉም መስክ ራሳችንን ለመቻል የጀመርነውን ጉዞ ለማሳካት ከፍተኛ አቅም አለን አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ ከምዕተ ዓመታት በፊት ለብዙ አፍሪካውያን የባቡር አገልግሎትን ያስተዋወቀው የኢትዮጵያ ምድር ባቡር በኋላም የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር አገልግሎት ለረጅም ዓመታት ግዙፍ ሀብቱን ይዞ ተቀብሮ የቆየ ተቋም ነበር ብለዋል።
ሀገራችን ቀድማ ጀምራ ኋላ የቀረችው መንግሥታት በተቀያየሩ ቁጥር አፍርሰው የመጀመር የመጥፎ ልማድ እስረኛ ሆና ለመቆየቷ አንዱ ማስረጃ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
የለውጡ መንግስት በተከተለው አዲስ ዕይታና በወሰደው ርምጃ የሀገር አንጡራ ሀብት የሆነው ተቋም፣ ባቡር እና የባቡር መሰረተ ልማት ከተቀበረበት ጥሻ ውስጥ ተፈንቅሎ እየወጣ ለመሆኑ በግቢው የሚታዩ ነገሮች ሁሉ በገፅታቸው ይታያሉ ነው ያሉት፡፡
የተደበቀው ሀብታችንን የመግለጥና የትናንት ወረትን ለሀገራዊ ብልፅግና የመጠቀም መርህን በማንገብ በተጀመሩ ሥራዎች የትራንስፖርት፣ የወርክሾፕና የጥገና ሥራዎች በለውጥ ሀዲድ ላይ ናቸው ብለዋል።
በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ስር ያለው የድሬዳዋ ደወሌ ባቡር አገልግሎት የተበተነውን ሠራተኛ በመሰብሰብ የቆሙ ባቡሮችን ጠግኖ ወደ ሥራ በማስገባት አሁን ላይ በሳምንት ሁለት ቀን አገልግሎት መስጠት በመጀመሩ ለትራንስፖርት ተደራሽ ያልሆኑ አካባቢዎችን ማገናኘት ተችሏል፡፡
በመጭው ዓመትም አገልግሎቱን ከሁለት ቀናት ከፍ ለማድረግ ዐቅዶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ለስኬቱ የፌደራል መንግሥት ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በሁሉም መስክ ራሳችንን ለመቻል የጀመርነውን ጉዞ ለማሳካት ከፍተኛ አቅም አለን ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በባቡር አገልግሎት ቀድመን ጀምረን ወደኋላ መቅረታችን ቢያስቆጭም ከራሳችን አልፎ አፍሪካን በባቡር ለማስተሳሰር በአዲስ ምዕራፍ በጋራ መሥራት ይጠበቅብናል ነው ያሉት።